ቀጥታ፡

ሴቶችን ወደ ከፍተኛ የአመራርነት ቦታ የማምጣት መልካም ተሞክሮን ማስፋት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ሴቶችን ወደ ከፍተኛ የአመራርነት ቦታ የማምጣት መልካም ተሞክሮን ወደ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ማስፋትና ቀጣይነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።

ለጠንካራ አገረ መንግስት ግንባታ ሴቶች ትውልድ ከመተካትና በስነ-ምግባር አንጾ ከማሳደግ የተሻገረ ሃላፊነት አለባቸው።

ከዚህ አኳያ በቤት ውስጥ የሥራ ጫና ሳይበገሩ የተሰጣቸውን የሥራ ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት አገርና ህዝብ የሚኮራበትን ሥራ የሚሰሩ በርካታ ሴቶች በምሳሌነት ይነሳሉ።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በተለይም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሴቶች የፖለቲካ አመራርና ተሳትፎ  ክፍል ኃላፊ ደሴት አበበ በአለምአቀፍ ደረጃ በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ ሴቶችን ወደ ከፍተኛ የአመራር ቦታ በማምጣት መልካም ተሞክሮ እንዳላት ያነሳሉ።


 

ይህን እርምጃ ወደ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ማምጣትና ቀጣይነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ከመንግስት ባለፈ እያንዳንዱ ተቋማዊ አደረጃጀት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ለሴቶች ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ትምህርት ወሳኝ ሚና እንዳለው ይናገራሉ።


 

በለውጥ ዓመታቱ በቅድመ አንደኛ፣በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት እርከኖች የሴቶችን የትምህርት ተደራሽነት ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች ውጤት አምጥተዋል ብለዋል።

ይሁንና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው የሴቶች ተሳትፎ ላይ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ይህን ችግር ለመፍታትም በሃላፊነት ላይ ያለን ሴቶች ወደ ፊት የማምጣቱን ስራ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲም አሁን ላይ በተለያየ ሥኬትና ሃላፊነት ላይ ያሉ ሴቶች ተተኪዎችን የማፍራትና አቅጣጫ የማሳየት ሃላፊነት አለባቸው ይላሉ።


 

በመሆኑም ይህን ተተኪዎችን የማፍራትና አቅጣጫ የማሳየት  ሃላፊነታቸውን በቀጣይ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት በረከት ወርቁ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በንግድ ዘርፉ የተሰማሩ ጀማሪ ነጋዴ ሴቶችን አቅጣጫ ሊያሳዩ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

በዚህ ረገድ ማህበራቸው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ነጋዴዎች የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሴቶች የፖለቲካ አመራርና ተሳትፎ ክፍል ኃላፊ ደሴት አበበ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የበለጠ ለማጎልበት ተቋማቸው የአቅም ግንባታ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም