ቀጥታ፡

ግብርን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል የተጀመረውን ልማት ለማሳካት ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው - ግብር ከፋዮች

ድሬደዋ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ ግብርን በወቅቱ እና በታማኝነት በመክፈል የተጀመረውን ልማት ለማሳካት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ግብር ከፋዮች ተናገሩ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ሐምሌ 17 እና 18 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ላይ  ለዘንድሮው በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈፀሚያ 14 ቢሊዮን 261 ሚሊዮን ብር በጀት ማፅደቁ ይታወሳል።

ከፀደቀው በጀት ውስጥም 10 ቢሊዮን 450 ሚሊዮን ብር አስተዳደሩ ከሚያመነጨው ኢኮኖሚ የሚሰበሰብ መሆኑም በወቅቱ ተመላክቷል።

ይህንን ተከትሎ የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን በዘንድሮ በጀት ዓመት 10 ቢሊዮን 450 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ  ዲጂታል ስርአትን በመዘርጋትእና የሰው ኃይል  ብቃትን ማሳደግ ላይ ለመስራት  ወደ ተግባር ገብቷል።

በጉዳዩ ላይ ለኢዜአ ያነጋገራቸው ነጋዴዎች እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ለግብር ከፋዮች ፈጣንና  ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል። 

ከግብር ከፋዮቹ መካከል ወይዘሮ ሰሚራ ሙባረክ እንደተናገሩት፤ ግብርን በታማኝነት መክፈልና የዜግነት ግዴታን መወጣት ዘመናዊነት ነው።


 

እኛ የምንከፍለው ግብር መልሶ ለተጀመረው አገራዊ ልማትና ለድሬዳዋ እድገት መሳካት የሚውል ነው ብለዋል።

ተቋሙ በየዓመቱ ለግብር ከፋዮች እየሰጠ የሚገኘው ቀልጣፋ አገልግሎቶች የሚያረኩ ናቸው ያሉት ደግሞ ሌላው ግብር ከፋይ አቶ ታደሰ ከተማ ናቸው።


 

አቶ ታደሰ እንዳሉት፤ ሁሉም ግብር ከፋይ ያለበትን ግብር በወቅቱ በታማኝነት በመክፈል ሊከተል ከሚችል ተጠያቂነት መራቅ ይኖርበታል።

አቶ አድነው አየለ በበኩላቸው ግብርን በወቅቱ መክፈል የተወጠኑ አገራዊና አካባቢያዊ የልማት ዕቅዶች በተገቢው ፍጥነትና ጥራት ተጠናቀው የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ያስችላሉ ብለዋል።


 

የተቋሙ ሠራተኞች ግብር ከፋዮች ሳይንገላቱ ግብርን ለመቀበል የሚያደርጉት ትጋት አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል ።

ወይዘሮ እመቤት አስራት በበኩላቸው የምንከፍለው ግብር መልሶ ለራሳችን መሠረተ ልማት ግንባታ የሚውል በመሆኑ ግብርን በወቅቱ በታማኝነት መክፈል የሁሉም ግብር ከፋይ ግዴታ ነው ብለዋል።


 

የገቢዎች ባለስልጣን የዘረጋቸውን አዳዲስ አሠራሮችና አደረጃጀቶች በየቅርንጫፉ በማስፋት የግብር ከፋዮችን እርካታ ይበልጥ ማሳደግ አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም