የአየር ንብረትና የምግብ ስርዓት ፤ በአዲስ አበባ ምክክር የሚደረግባቸው የአፍሪካ አንገብጋቢ አጀንዳዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረትና የምግብ ስርዓት ፤ በአዲስ አበባ ምክክር የሚደረግባቸው የአፍሪካ አንገብጋቢ አጀንዳዎች
ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ማግስት በአፍሪካ አበይት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እና አምስተኛ የድህረ ምርት ጉባኤ እና አውደ ርዕይ በመዲናዋ ይካሄዳሉ።
እነዚህ ተከታታይ አህጉራዊ ከፍተኛ የምክክር መድረኮች አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና ለምግብ ስርዓት መጠናከር የሰጠችውን ትኩረት ከማሳየት ባሻገር የኢትዮጵያ በአጀንዳዎቹ ላይ በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ እያደገ የመጣውን የመሪነት ሚና ያመላክታሉ።
አየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ስርዓት እርስ በእርሳቸው የተጋመዱ የአፍሪካ ፈታኝ የልማት ጉዳዮች ናቸው። ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል። ጉባኤው በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ህብረት የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነው። “የአረንጓዴ ጉዳይ ውይይቶች አረንጓዴን ማዕከል ያደረጉ እርምጃዎች” የሁነቱ መሪ ሀሳብ ነው።
ጉባኤው እ.አ.አ በ2023 በኬንያ በተካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ውጤቶች ላይ በመመርኮዝ የሚወያይ ሲሆን በተለይም የናይሮቢ ድንጋጌ አፈጻጸምን ይገመግማል። ድንጋጌው የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ የተግባር ምላሽ እንዲፋጥኑ እና የዓለም ሀገራት የገቡትን የፋይናንስ ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲሰጡ ጥሪ የቀረበበት ነው።
አፍሪካ ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ከሶስት እስከ አራት በመቶ የሆነ ዝቅተኛ ድርሻ ቢኖራትም ዋንኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ አህጉር ሆናለች።
አህጉሪቷ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እና ለማቋቋም እንዲሁም የማጣጣሚያ እቅዶችን ለመተግበር በየዓመቱ 250 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልጋት መሆኑ ቢገለጽም እያገኘች ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ግን 30 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው።
በጉባኤው የበለጸጉ ሀገራት የገቡትን የፋይናንስ ድጋፍ ተደራሽ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ።
በተጨማሪም ጉባኤው ከህዳር 1 እስከ ህዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም በብራዚል ቤለም በሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) ላይ አፍሪካ ይዛቸው በምትቀርባቸው የጋራ አጀንዳዎች ላይ ምክክር ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከማስተናገድ ባሻገር አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአረንጓዴ ልማት ስኬታማ ተሞክሮዋን እንደምታቀርብ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ያላትን የመሪነት ሚና የምታጠናክርበት ጉባኤ እንደሆነም ተመላክቷል።
መድረኩ በሀገራት መሪዎች ደረጃ ልዩ ልዩ ውሳኔዎች ይተላለፍበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን እስከ 25 ሺህ የሚደርሱ እንግዶች በዚህ ጉባኤ እንደሚታደሙ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ጉባኤው እያንዣበበ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ለመቀልበስ ሀገራት ዳግም ቁርጠኝነታቸውን የሚያረጋግጡበት እንደሆነም ተነግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ጉባኤውን አስመልክቶ አስተላለፈውት በነበረው መልዕክት ምድረ ቀደምት የሆነችው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እንደምታስተናግድ ገልጸዋል።
ጉባኤው የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ስትራቴጂ ለመደገፍ ቁልፍ የሆኑ ተፈጥሮ ተኮር መፍትሄዎች እንደሚቀርቡ አመልክተዋል።
አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጨባጭ ለሆኑ ተግባራዊ መፍትሄዎች ያላትን የጠለቀ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ የሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተሳታፊዎችን ለመቀበል ተዘጋጅታለች ሲሉም ገልጸዋል።
ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዋና ጉባኤውን አስመልክቶ የተዘጋጁ ቅድመ ውይይቶች ይደረጋሉ።
ሌላኛው አህጉራዊ ሁነት አምስተኛው የአፍሪካ የድህረ ምርት ብክነት ቅነሳ ጉባኤ እና አውደ ርዕይ ነው። ጉባኤ እና አውደ ርዕይ “ ምርትን መጠበቅ፤ የድህረ ምርት ብክነት አስተዳደር መፍትሄዎች ለማይበገር እና ሁሉን አካታች የምግብ ስርዓት” በሚል መሪ ሀሳብ ይደረጋል።
ጉባኤው በአፍሪካ የድህረ ምርት ብክነትን በፍጥነት መቀነስ እንዲሁም ዘላቂ የግብርና እና የምግብ ስርዓቶችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ እንደሚመክር የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።
አይበገሬነት፣ ኢኖቬሽን እና የምግብ የቆይታ ጊዜ ማራዘም ውይይት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።