ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ የስታትስቲክስ ዘርፍ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም እና በአፍሪካ የልማት ባንክ ድጋፍ  በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎትና በኮሪያ ስታትስቲክስ  መካከል የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ትብብር መርኃ ግብር ተካሂዷል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ ያላቸው ግንኙነት ከልማት አጋርነት ከፍ ያለና ታሪካዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው ይህንኑ እድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ጥራት ያለው የስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ ቀደም ብለው በስታትስቲክስ አቅም ግንባታ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

የተቋም ግንባታ፣ የሰው ኃይል ልማትና የስታትስቲክስ መረጃ አሰባሰብ ላይ ልምድ መለዋወጥ የስምምነቱ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ ወደ ተግባር እንዲቀየር ከፋይናንስ ተቋማት እና ለጋሽ ድርጅቶች የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልግ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ዛሬ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር ለዚሁ ዓላማ የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ በሚያደርጉበት ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ልማት ባንክ የስታትስቲክስ ከፍተኛ ባለሙያ ቪንሰንት ንገንዳኩማና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በስታቲስቲክስ ዘርፍ እያከናወነችው ያለው ተግባር አበረታች ነው ብለዋል፡፡


 

ይህን አጠናክራ እንድትቀጥል ባንኩ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስታትስቲክስ መረጃ አሰባሰብ ስርዓት ጠንካራ አቅም እየገነባች መምጣቷን የተናገሩት በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢኮኖሚ አማካሪ አሊ ዛፋር ናቸው፡፡


 

ኢትዮጵያ በትብብሩ በመደገፍ የመረጃ አያያዝ ስርዓቷን የበለጠ እንደምታሻሽል ያላቸውን እምነት ጠቅሰው፤ የተመድ የልማት ፕሮግራም የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኮሪያ ስታትስቲክስ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኦህ ሶንግቸኦል በበኩላቸው፤ ተቋማቸው ኢትዮጵያ በስታቲስቲከስ ዘርፍ የምታከናውነውን ተግባር ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም