ቀጥታ፡

20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በሚያጎላ መልኩ ይከበራል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2017(ኢዜአ)፦20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት"  በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በሚያጎላ መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ የሚከበረው የ20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር መሪ ዕቅድ ላይ የአብይ ኮሚቴ ውይይት አካሂዷል። 


 

አብይ ኮሚቴው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር መነሻ መሪ እቅድና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አከባበር እቅድ ላይ ውይይት ተካሂዶ አፅድቋል።   

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚህ ወቅት እንዳሉት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አንድነትና ወንድማማችነት የሚረጋገጥበት በዓል ነው። 

የ2018 ዓ.ም በዓል ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የማንሰራራት ጉዞን የጀመረችበትና ውጤትም እየተመዘገበበት ባለበት ወቅት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚመረቅበት እንዲሁም አገራዊ የምክክር ሂደቱ በተደራጀ አግባብ በሚጀመርበትና ሌሎች በርካታ ኹነቶች በሚካሄዱበት ወቅት መከበሩም በዓሉን ልዩ የሚያደርገው መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዓሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚከበር መሆኑን አንስተው፤ ይህም የክልሉን የልማት ስራዎች፣ ለመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት መነቃቃት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በዓሉ "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ  የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በሚያጎላ መልኩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንደሚከበር ገልፀዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ዘሀራ ሁመድ በበኩላቸው፤በዓሉ ትስስርና አብሮነትን የበለጠ በሚያጠናክሩ ኹነቶች ይከበራል ብለዋል።  


 

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገመንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ባንቺይርጋ መለሰ በበኩላቸው በዓሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ከህዳር 1 ጀምሮ ይከበራል ብለዋል።


 

የማጠቃለያ መርሃግብሩም ከህዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የማጠቃለያ መርሃግብር እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

ህዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ህዳር 26 የአብሮነት ቀን፣ ህዳር 27 የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቀን፣ ህዳር 28 የምክክር ቀን፣ ህዳር 29 የኢትዮጵያዊያን ቀን ተብለው በተለያዩ ኹነቶች እንደሚከበሩም ተናግረዋል።

ክልሉ አቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም በዓሉን ለማስተናገድ የሚያስችለውን ዝግጅት ሲያከናውን መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ናቸው።


 

በክልሉ ያሉ ሰባቱ ክላስተር ከተሞችን በዓሉን ለማስተናገድና እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም