ጉምሩክ ኮሚሽን ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጉምሩክ ኮሚሽን ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ገለጹ።
ኮሚሽኑ የአዲስ ሠራተኞች የሥልጠና ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ኮሚሽኑ፥ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ሥነ-ምግባር የተላበሱ እና ትጉህ ባለሙያዎችን ማፍራት፣ ዘመኑን የዋጁ አሠራሮችና ደንቦችን ማዘጋጀት እና ተቋሙን በቴክኖሎጂ የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑን በብቁ የሰው ኃይል ይበልጥ ለማደራጀት በተያዘው ግብ መሰረት ከመላ ሀገሪቱ የተወጣጡ ከ3 ሺህ በላይ አዲስ ሠራተኞች ወደ ተቋሙ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።
የንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ የሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ንግድ ስርዓት ላይ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ የመከላከልና የቁጥጥር ሥራዎች ቅንጅትን ማጠናከርን የሚጠይቁ መሆናቸውን አንስተዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም አዲስ የተመደቡ ሠራተኞች ተቋሙና ሀገር የምትሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸው አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጀመረችው ገቢን የማስፋት ሥራ እና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ጠንካራና ብቁ የጉምሩክ ባለሙያ ይፈልጋል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ዩኒቨርሲቲው ለሰው ኃይል አቅም ግንባታ የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።