ቀጥታ፡

በአማራ ክልል 255 ሺህ ሄክታር መሬት በቅመማቅመም ፣አትክልት እና ስራስር ሰብል ለምቷል

ባህርዳር ፤ ነሐሴ 5/2017 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል  በተያዘው የመኸር ወቅት  255 ሺህ ሄክታር መሬት   በቅመማቅመም ፣ አትክልት እና የስራስር ሰብል ማልማት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ  የመስኖ እና ሆልቲ ካልቸር ልማት ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመኸሩ  ወቅት 286 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ በቅመማቅመም፣ አትክልትና ስራስር ሰብል ለማልማት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።


 

ከዚህም እስካሁን  255 ሺህ ሄክታሩ መሬት በበርበሬ፣ ጥቁርና ነጭ አዝሙድ፣ በአብሽ፣ በነጭና ቀይ ሽንኩርት እንዲሁም በድንች ሰብል  መልማቱን አስታውቀዋል።

ከለማው መሬት  ውስጥም  ከ74 ሺህ 100 ሄክታር የሚበልጠው በኩታ ገጠም  የተከናወነ  መሆኑን አስረድተዋል።

በልማቱም ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አመልክተዋል። 

ቀሪው መሬት በቀጣይ ነጭና ጥቁር አዝሙድን ጨምሮ ሌላም የቅመማቅመም ሰብል  ዘር እንደሚሸፈን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ አጠቃላይ ከሚለማው 31 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ  አስታውቀዋል።

አርሶ አደር ማሬ መኮንን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣቁሳ ወረዳ  ነዋሪ ሲሆኑ፤ ቀደም ሲል ጀምሮ የቅመማቅመም ምርትን በጥራትና በብዛት አምርተው ለገበያ በማቅረብ  ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅትም አንድ ሄክታር ከሚጠጋ መሬት ላይ እያለሙት ካለው በርበሬና ጥቁር አዝሙድ የተሻለ ምርት ለማግኘት ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በበርበሬ ቅመማቅመም ሰብል እያለሙት ካለው ሁለት ሄክታር ከሩብ መሬት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር መኳንንት አወቀ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ያመረቱትን በርበሬ፣ ነጭና ጥቁር አዝሙድ ለገበያ በማቅረብ በተሻለ ዋጋ ሽጠው ተጠቃሚ እንደሆኑም አውስተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የወንበርማ ወረዳ አርሶ አደር አባይ ሞላ በበኩላቸው፤  በዘንድሮው የመኸር ወቅት አንድ ሄክታር መሬት በርበሬ  እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

እያለሙት ካለው የበርበሬ ሰብል በቀጣይ የተሻለ ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ ሰብሉን እየተንከባከቡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ከግብርና  ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤  ባለፈው የመኸር ወቅት በክልሉ በቅመማቅመም፣ አትክልትና ስራስር ሰብል  ከለማው 274 ሺህ ሄክታር መሬት 28 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም