ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳየነውን አንድነትና ህብረት አጠናክረን እናስቀጥላለን-የኢሉ አባቦር ዞን ነዋሪዎች

መቱ፤ነሐሴ 5/2017 (ኢዜአ)፦በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳየነውን አንድነትና ህብረት አጠናክረን እናስቀጥላለን ሲሉ የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በዛሬው ዕለት ኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ ሲደርስ በዞኑና በከተማው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።


 

በዋንጫ አቀባበሉ ላይ ከተገኙት የዞኑ ነዋሪዎች መካከል የሁሩሙ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጀናቶ ታደሰ እንዳሉት፥ የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በተለያየ መልኩ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል።


 

የአካባቢያቸው ነዋሪዎችም ያለ አንዳች ልዩነት በሀገር ፍቅር ስሜት ለግድቡ ግንባታ የአቅማቸውን ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደነበረ ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ ሂደት ወደ ፍጻሜው ምዕራፍ መድረሱ መሰማቱን ተከትሎ አሁንም በቦንድ ግዥ ተሳትፎአቸውን እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

''በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳየነውን አንድነትና ህብረታችንን በሌሎች የልማት ስራዎችም ማጠናከር ይጠበቅብናል'' ሲሉም አቶ ጀናቶ ተናግረዋል።

የመቱ ከተማ ነዋሪው አቶ ዘላለም ታደሰ በበኩላቸው፥ የህዳሴ ግድብ አንድነታችን በከፍተኛ ደረጃ የተንጸባረቀበት ግድባችን ነው ብለዋል።


 

ለግድቡ ግንባታ እንደ አንድ በመሆን ያደረግነው ተሳትፎ ሌሎች የልማት ስራዎቻችንን በጋራ ሆነን ማረጋገጥ እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ዜና እስከሚሰማበት ዕለት በቀሩት ቀናትም ተሳትፏቸውን የሚቀጥሉ መሆናቸውን አክለዋል።

የኢሉአባቦር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ሰንበታ ዋቁማ፣ የጸጥታ አካላት በሰላምም ሆነ በልማት መረጋገጥ እያደረጉ ያሉት ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ለፍጻሜ እስከሚደርስ ድረስ የዞኑ ጸጥታ አካላት ባልደረቦቻቸውን በማስተባበር የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

በግድቡ ግንባታ የመጨረሻ አሻራቸውን ለማኖር የፖሊስ አባላት የቦንድ ግዥና የድጋፍ ተሳትፎ እንደሚጠናከር የገለጹት ደግሞ የመቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አብዱራዛቅ ነጋ ናቸው።

በብልጽግና ፓርቲ የኢሉባቦር ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞሲሳ ለሜሳ በበኩላቸው፥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተደረገው የሕብረተሰቡ ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።


 

''ግድቡ የሀገራዊ አንድነታችን ማሳያ ነው'' ያሉት ኃላፊው የግድቡ ዋንጫ ወደ ዞኑ መምጣቱን ተከትሎ የዞኑ ህዝብ በተነቃቃ መንፈስ ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም