ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የተከናወኑት ተግባራት ስኬታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የተከናወኑት ተግባራት ስኬታማ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2017(ኢዜአ)፦ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ወደ ውጭ በሚላኩና ወደ ሀገር በሚገቡ የግብርና ምርቶች ላይ የጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ያደርጋል።
የቁጥጥር ስራው የግብርና ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የተመዘገቡና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዲሪባ ኩማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የግብርና ምርቶች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ግብዓቶች እና አገልግሎቶች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር ሲያከናውን ቆይቷል።
በዚህም በ2017 በጀት አመት ወደ ውጭ በተላኩ የግብርና ምርቶች ግብይት ላይ ከጥራት እና ከደህንነት አንፃር ችግሮች እንዳልገጠሙ ገልፀዋል።
በበጀት ዓመቱ 877 ሺህ 350 ቶን ዕፅዋት እና የዕፅዋት ውጤቶች፤ 21 ሺህ 200 ቶን ስጋና ተረፈ ምርት፣ 621 ሺህ የቁም እንስሳት፣ 270 ቶን ሰምና የማር ምርቶች የቁጥጥርና የክትትል ስራ ከተካሔደባቸው ምርቶች መካከል ናቸው ብለዋል።
የቁጥጥር ስራዎቹ በአለምአቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ መካሄዳቸው ለውጤት መገኘት መሰረት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የቁጥጥር ስራው መጠናከር ወደ ውጭ የሚላኩ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ተፈላጊነት ከእለት ወደ እለት እንዲጨምር እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ባለስልጣኑ በእንስሳት እርባታ፣ በአበባ እና በዕፅዋት እርሻ ላይ የማዳበሪያና የኬሚካል አጠቃቀምን ጨምሮ የምርት ጥራትን እንደሚከታተልም አብራርተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ሚሊዮን ኩንታል በሚጠጋ ምርጥ ዘር ላይ የጥራት ቁጥጥር በማድረግ ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ መደረጉን በመግለጽ።
የግብርና ምርቶች ላይ የሚካሔደው የቁጥጥር ስራ በዋናነት የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማሟላት ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።
ቁጥጥር ተግባሩን ተከትሎ የእንስሳት ሃብቱ ከቀደመው በተሻለ አለምአቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ እያስቻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሚሌ የተገነባው የእንስሳት ኳራንቲን /ማቆያ / አለምአቀፍ ተቀባይነት ማግኝቱን ተከትሎ በርካታ የቁም እንስሳትን ወደ ተለያዩ ሀገራት መላክ መቻሉንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማሕበር የቦርድ ፕሬዚዳንት ከሊፋ ሁሴን በበኩላቸው፤ ማህበሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 120 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ስጋና ተረፈ ምርቶች ወደ ውጭ መላኩን አስታውቀዋል።
ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 67 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
ስኬቱ ሊመዘገብ የቻለው ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራታቸውን እንዲጠብቁ በተከናወኑት ተግባራት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የአሰራር ስርዓት ጠንካራ መሆን በመዳረሻ አገራት ተቀባይነትን ከማስገኘቱ ባለፈ ተጨማሪ ገበያዎችን ለማግኘት ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በመላው ሀገሪቱ 45 ኳራንቲን እና 4 የምርት መመርመሪያ ማዕከላት እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።