ቀጥታ፡

ወጣቶች የምስራቅ አፍሪካ የሰላም አጀንዳ መሪ መሆናቸው ለዘላቂ ቀጣናዊ መረጋጋት ቁልፍ ሚና አለው - ኢጋድ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2017(ኢዜአ)፦ ወጣቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አስታወቀ።

የመጀመሪያው የኢጋድ ቀጣናዊ የወጣቶች የሰላም እና ደህንነት ኮንፍረንስ ነሐሴ 7 እና 8 ቀን 2017 ዓ.ም በኬንያ ናይሮቢ ይካሄዳል።

ወጣቶች ከፍተኛ የለውጥ ኃይል ናቸው ያለው ኢጋድ ሰላማዊ እና ሁሉን አሳታፊ መጻኢ ጊዜ የመፍጠር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ገልጿል።

በኮንፍረንሱ በኢጋድ አባል ሀገራት በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ወጣት መሪዎች በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው።

ወጣቶቹ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ያስችላሉ ያሏቸውን የመፍትሄ ሀሳቦች እንደሚያቀርቡ ኢዜአ ከኢጋድ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በውይይቱ ላይ ስደተኛ ወጣቶችም እንደሚሳተፉና በቀጣናዊ የሰላም ምላሽ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ያካፍላሉ።

ኮንፍርንሱ ወጣቶች ለቀጣናዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት የሀገራት ኢኒሼቲቮችን በተቀናጀ መልኩ ለመተግበር ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት እንደሆነም ተመላክቷል።

ወጣቶች የምስራቅ አፍሪካ የሰላም አጀንዳ መሪ እና መሐንዲስ መሆናቸው ለዘላቂ ቀጣናዊ መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንዳለው ነው ኢጋድ ያስታወቀው።

ኢጋድ እ.አ.አ በ2021 በዩጋንዳ ኢንቴቤ ባደረገው ስብሰባ የኢጋድ የወጣቶች የሰላም ፎረምን ይፋ ያደረገ ሲሆን ፎረሙ ወጣቶች በቀጣናው ሰላም፣ ደህንነትና መረጋጋት ላይ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ያለመ ነው።

ወጣቶቹ በፎረሙ አማካኝነት ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከል እና የድህረ ግጭት አስተዳደር ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም