ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት ሴቶች የተመደቡባቸው ተቋማትን በብቃት በመምራት በአርዓያነት የሚጠቀስ ሥራ አከናውነዋል-አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4/2017(ኢዜአ)፦በለውጡ ዓመታት ሴቶች የተመደቡባቸው ተቋማትን በብቃት በመምራት በአርዓያነት የሚጠቀስ ሥራ ማከናወናቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ሴቶች ከየት ወዴት" በሚል ሃሳብ የለውጡ ትሩፋት የሆኑ ሴት አመራሮች መድረክ በሳይንስ ሙዚዬም ተካሂዷል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ ያለ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የፖለቲካ ተሳትፎ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል።

የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ላመረጋገጥ የሴቶችን ጉዳይ በልማት ዕቅዶች ውስጥ ማካተት እንደሚገባ ገልጸው፤ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

የሴቶችን የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማጎልበት የተሰሩ ውጤታማ ስራዎችን የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በለውጡ ዓመታት በሴቶች ላይ የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶችን በመቀየር በሌማት ትሩፋትና በስራ ዕድል ፈጠራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


በኢትዮጵያ የዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አውድ በመፍጠር የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ ተቋማዊ አደረጃጀት መፈጠሩን ተናግርዋል፡፡

ሥርዓተ ፆታን በማመጣጠን የሴቶችን መሪነትና ውሳኔ ሰጭነት ሚና ማሳደግ በመቻሉ ገልጸው፤ በለውጡ ዓመታት የተመደቡባቸው ተቋማትን በብቃት መርተው አርዓያነታቸውን አሳይተዋል፤ ኢትዮጵያም ተጠቅማለች ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት የሰጡት አመራር ለሌሎች ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሴቶችን መብት ማስከበርና ተሳትፏቸውን ማረጋገጥ የሚቻለው ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሲኖር መሆኑን በመጥቀስ፤ ሴት ከፍተኛ አመራሮች ተተኪዎችን ለማፍራት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡


ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ ሴቶች የአመራርነት ብቃታቸውን የሚያሳድጉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በመስራታቸው መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ የአመራር ቋት መዘጋጀቱም ለተገኘው ውጤት መሰረት ሆኗል ብለዋል፡፡

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግ ለሴት አደረጃጀቶች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ሴቶች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ በሌማት ትሩፋትና በንግድ ዘርፎች የሚሳተፉበት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ የሴቶች ተሳትፎ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም