የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ገለጹ።
በተለያየ ሙያ ላይ የተሰማሩ የመንግስት ከፍተኛ ሴት ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ሴቶች ፈተናዎችና ዕድሎች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት አካሂደዋል።
የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ከፓናሉ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት ሥራ አስፈጻሚ ሳባ ገብረመድህን፤ የሴቶችን ተደራራቢ ሥራ በመቀነስ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በአሁን ወቅት መንግስት በተለይም የሴት ሰራተኞችን ጫና ለመቀነስ የልጆች ማቆያ ማዘጋጀቱ ለበርካታ ሴቶች እፎይታ የሰጠና የሥራ ውጤታማነታቸውን ያጎለበት ነው ብለዋል።
ሌላዋ የፓናሉ ተሳታፊ በተባበሩት መንግስታት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ የሥነ ተዋልዶ ባለሙያ የሆኑት ቲኖስ ከበደ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚታየውን የተዛባ አመለካከትና ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ለማስቀረት የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የሴቶችን የፋይናንስ አካታችነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም ካለው ፍላጎት አኳያ የበለጠ መስራት እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ ሌላዋ የፓናሉ ተሳታፊ የእናት ባንክ ከፍተኛ የፋይናንስ ባለሙያ ትዕግስት አባተ ናቸው።
በተባበሩት መንግስታት የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ፕሮግራም ባለሙያ ደሴት አበበ በበኩላቸው፥ ሴቶች ወደ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊትና ከመጡም በኋላ የተለያዩ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል ነው ያሉት።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖሊሲ፣የምርምርና ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ ትፍሰት ሰለሞን (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ሴቶች በማህበራዊና በኢኮኖሚ ተሳትፏቸው እያደገ መምጣቱን ነው የተናገሩት።
ይሁን እንጂ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።