ቀጥታ፡

የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና አለው -ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4/2017(ኢዜአ)፦ዲጂታል መታወቂያ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንዳለው በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የሕግና ፖሊሲ ክፍል ኃላፊ ገብሬላ አብርሃም ገለጹ፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ሴቶች ከየት ወዴት" በሚል ሃሳብ የለውጡ ትሩፋት የሆኑ ሴት አመራሮች መድረክ በሳይንስ ሙዚዬም እየተካሄደ ነው፡፡

በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የሕግና ፖሊሲ ክፍል ኃላፊ ገብሬላ አብርሃም በመድረኩ ላይ "ሴቶችና ብሄራዊ መታወቂያ" በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ኃላፊዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ያለ ሴቶች ተሳትፎ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡

በለውጡ ዓመታት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዲጂታል መታወቂያ ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገትና የተሳለጠ አገልግሎት አሰጣጥ የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ዲጂታል መታወቂያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ገቢራዊ ከተደረገ በኋላ አገልግሎት አሰጣጡን ግልጽና ቀልጣፋ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ21 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸውንና ከ55 በላይ ተቋማት በፋይዳ መተሳሰራቸውን ገልፀዋል፡፡

ለዲጂታል መታወቂያ ከተመዘገቡት መካከል 40 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሴቶችን የተሳትፎ ከዚህም በላይ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ለሴቶች ሕጋዊ ዋስትና የሚሰጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን ለማጎልበት ሚናው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ሴት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሴቶች በዲጂታል መታወቂያ ላይ በቂ መረጃ ኖሯቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር አለባቸው ብለዋል፡፡

መንግስት ለዲጂታል መታወቂያ በሰጠው ትኩረት ቴክኖሎጂውን በአገር ውስጥ ማልማትና ገቢራዊ ማድረግ የሚችልበት የፋይናንስ ድጋፍ እያገኘ መሆኑን በማንሳት፤ በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል "ፋይዳፖስ" የተሰኘ መተግበሪያ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዲጂታል መታወቂያ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያስመዘገበችው ውጤት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ልምድ ለመቅሰም እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም