ቀጥታ፡

መንግስት የሴቶችን የአመራርነት እና ውሳኔ ሰጪነት ሚና የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 4/2017 (ኢዜአ)፡-መንግስት የሴቶችን የአመራርነት እና ውሳኔ ሰጪነት ሚና የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ልዩ ዕውቅና ተሰጥቷል።

ዕውቅናው የተሰጠው በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የከፍተኛ ሴት አመራሮች የምክክር መድረክ ነው።


 

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መንግስት የሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የፖለቲካ ተሳትፎ ካልተረጋገጠ  ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል ያምናል ብለዋል።

የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በልማት ዕቅዶች ውስጥ የሴቶችን ጉዳይ በማካተት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን በማምጣት የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

የሴቶችን የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ጠቅሰው፣በቀጣይም ይህን ተሳትፎ የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያስታወቁት።


 

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሌማት ትሩፋት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና፣ በሴቶች ላይ የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶችን በመቀየር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሁሉንም ዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሙሉ ዕይታ መፈጠሩንም ጠቅሰው፤ በዚህም የሴቶችን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲፈጠር መደረጉንም አንስተዋል።

መንግስት የሴቶችን መብትና ተሳትፎ ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ማረጋገጥና የሴቶችን የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚና የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ  የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለተሰጠው ልዩ ዕውቅና ምስጋና አቅርበዋል።

"ሴት አመራሮች ለኢትዮጵያ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ መድረኩን ያዘጋጀው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም