በመዲናዋ ትውልዱን የሚያኮራ ተምሳሌታዊ ስራ ተከናውኗል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ትውልዱን የሚያኮራ ተምሳሌታዊ ስራ ተከናውኗል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ ትውልዱን የሚያኮራ ተምሳሌታዊ ስራ መከናወኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትላንትናው እለት በፒያሳ መልሶ ማልማት፣ በ4 ኪሎ እንጦጦ፣ጉለሌ የእፅዋት ማዕከል የኮሪደር ልማትና የእንጦጦ ወዳጅነት አደባባይ ፒኮክ ፓርክ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ስራ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅናና የምስጋና መርሀግብር ተከናውኗል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ስራ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በፒያሳ መልሶ ማልማት፣ በ4 ኪሎ እንጦጦ፣ ጉለሌ የእፅዋት ማዕከል የኮሪደር ልማትና የእንጦጦ ወዳጅነት አደባባይ ፒኮክ ፓርክ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የተከናወነው ስራ ሀገር የምትገነባው በልጆቿ ነው የሚለውን በተጨባጭ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የኮሪደር ልማት ልብን የሚያሞቅ ስራ የተከናወነበት መሆኑን ገልጸው፤ ልማቱ ለበርካታ ዜጎች እፎይታን የፈጠረ ነው ብለዋል።
ለግንባታው ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉ እጆች የሚመሰገኑ መሆናቸውን ገልጸው የምንገነባው የጋራ ሀገራችን እና ክብራችንን ነው ብለዋል።
መጪዉ ትውልድና መላዉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሚኮራበትን አስደናቂ ስራ መሰራቱን አመላክተዋል።
ልማቱ በኢትዮጵያ ልጆች ዲዛይነርነት፣ አርክቴክትነት፣መሪነትና አስተባባሪነት በታሰበው ልክና በአጭር ጊዜ ዉስጥ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ አሳክተናል ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ እና የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአራት ኪሎ ሽሮሜዳ ያለው አካባቢ በርካታ ተቋማት ያሉበት ነገር ግን ይህንን የሚመጥን ልማት እንዳልነበረው ተናግረዋል።
በዚህ አካባቢ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ቦታውን የሚመጥን ግንባታ መከናወኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ኮሪደር ልማቱ ቀጣይነት ያለው የስራ እድል በሚፈጥር መንገድ መከናወኑን ተናግረዋል።