የለውጥ ሥራዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ የሴቶች ተሳትፎ የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የለውጥ ሥራዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ የሴቶች ተሳትፎ የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4/2017 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ይበልጥ ፍሬያማ እንዲሆኑ የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለፁ።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሴት አመራሮች የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሀላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ሴት አመራሮች፤ አምባሳደሮች የግል ዘርፉ ተወካዮችና የሴት አደረጃጀት ተወካዮች ታድመዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች ሴቶች ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ያሳዩት ተግባራዊ ቁርጠኝነት በርካታ ሴቶች በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ተሰማርተው ውጤታማነታቸውን እንዲያሳዩ ዕድል መፍጠሩንም አስታውሰዋል።
ሴቶች ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥና ለአገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው ባለፋት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች ምስክር መሆናቸውን ነው የገለፁት።
በአስር አመቱ የልማት ዕቅድ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የተያዘውን ግብ እውን ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሴቶች እስካሁን የነበረንን አስተዋፅኦ የበለጠ ለማሳደግ መትጋት አለብን ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ የሴቶች ተሳትፎ የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ነው ሚኒስትሯ ያረጋገጡት።
"ሴት አመራሮች ለኢትዮጵያ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ከፍተኛ የሴት አመራሮች መድረክ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የፓናል ውይይቶች ይደረጋሉ።