ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የነፃ ትምህርትና ስልጠና ዕድል ተጠቃሚ በመሆናችን ኩራት ይሰማናል - ደቡብ ሱዳናዊያን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 4/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የነፃ ትምህርትና ስልጠና ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያሳድገው ደቡብ ሱዳናዊያን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት ተማሪዎች ገለጹ። 

ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለጎረቤት ሀገራት ዜጎች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ላይ ትገኛለች።  

የጎረቤት ሀገራት ዜጎችም  በዕድሉ በመጠቀም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ዕውቀትና ክህሎታቸውን እያዳበሩ ይገኛሉ።

የነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ የሆኑት ደቡብ ሱዳናዊያኑ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ካም ዊሊያም እና የ3ኛ ዓመት የሜዲስን ተማሪ ስቲፈን ቻፕሊ ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ደቡብ ሱዳናዊያኑ ተማሪዎቹ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የክረምት ወራት የሳይበር ታለንት ባለተሰጥኦ ስልጠና ተጠቃሚ ሆነዋል።

ኢዜአ ካም ዊሊያም እና ስቲፈን ቻፕሊንን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተገኝቶ የሳይበር ደኅንነት ሥልጠናን አስመልክቶ አነጋግሯል።

ተማሪዎቹ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ዜጎች የምትሰጠው የነፃ ትምህርት ዕድል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ለቀጣናው ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። 

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ካም ዊሊያም÷ ኢትዮጵያ ሀገሩንና ወገኑን በዕውቀትና ክህሎት ማገልግል የሚችልበትን ነፃ የትምህርት ዕድል እንደሰጠችው ገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የክረምት ወራት የሳይበር ታለንት ባለተሰጥኦ ስልጠና የሶፍት ዌር ዴቨሎፕመንት ስልጠና እየተከታተለ መሆኑን ተናግሯል።


 

ኢትዮጵያ ለሰጠችው የነፃ ትምህርትና የሳይበር ደኅንነት የክህሎት ስልጠናም ምስጋና አቅርቧል።

በቀጣይም ትምህርቱን ተከታትሎ ወደሀገሩ ሲመለስ የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲሚወጣ አስታውቋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የሜዲሰን ተማሪ ስቲፈን ቻፕሊ÷ ኢትዮጵያ ከሰጠችኝ ነፃ የትምህርት ዕድል በተጓዳኝ የክረምት ወራት የሳይበር ደኅንነት ስልጠና እየተከታተልኩ ነው ብሏል።


 

የሳይበር ደኅንነት ስልጠናው ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጓዳኝ የሳይበር ክህሎታቸውን ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለደቡብ ሱዳናዊያን የሚሰጡት ነፃ የትምህርት ዕድል የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሚደረግ ድጋፍ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም