ቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ልጆቻችንን በሳይንሳዊ መንገድ እንድናሳድግ ዕድል ፈጥሮልናል-ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
ቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ልጆቻችንን በሳይንሳዊ መንገድ እንድናሳድግ ዕድል ፈጥሮልናል-ተጠቃሚዎች

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4/2017 (ኢዜአ)፡-የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ሳይንሳዊ የልጅ አያያዝ እውቀትን በማስጨበጥ በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ ልጆች እንዲያሳድጉ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው የመርሃግብሩ ተጠቃሚ እናቶች ተናገሩ፡፡
የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ከጽንስ እስከ ስድስት ዓመት ዕድሜ ያሉ ሕጻናት በአዕምሮ እና በአካል እንዲበለጽጉ የማድረግ ዓላማን አንግቦ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡
በዚህም እናቶች፣ አሳዳጊዎች እና ባለድርሻ አካላት በሕጻናት አስተዳደግ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየተሰራ ሲሆን ብቁ ትውልድ ለመገንባትም መርሐ ግብሩ ወሳኝ ነው፡፡
የአዲስ አበባ በቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም ትግበራ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሞክሮ ማዕከል ሆናለች፡፡
ቀዳማይ ልጅነት ላይ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ለእናቶች፣ አሳዳጊዎች እና ወላጆች ትልቅ ፋይዳ እያስገኘላቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመርሐ-ግብሩ ተጠቃሚ እናቶች ተናግረዋል፡፡
ከአስተያያት ሰጪዎች መካከልም ወይዘሮ ኃይማኖት ሁንልኝ እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም በርካታ እንክብካቤና ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ከእርግዝና ጊዜያቸው ጀምሮ ለልጃቸው በሚደረግላችው አስፈላጊውን ግንዛቤ በማግኘታቸው እንክብካቤ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ባለሙያዎች ወደ ቤታቸው እየመጡ በሚሰጧቸው ምክር፣ ድጋፍና እንክብካቤ ጠንካራ ስነ-ልቦና ገንብተው ልጆቻቸውን በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ጸሐይ ግርማ ናቸው።
የቀዳማዊ ልጀነት ልማት ፕሮግራም የድጋፍና የክትትል ባለሙያ ሰላም ጣፋ በበኩሏ እንደገለጸችው፤ መርሐ ግብሩ ለወላጆች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች እፎይታን የሚሰጥ ነው።
በመርሐ ግብሩ ከሁለት ዓመታት በላይ ለበርካታ ወላጆች ከእርግዝና ጊዜ ጀምሮ ልጆች 6 ዓመት እስኪሞላቸው ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጻለች፡፡
በዚህም ህጻናት ጤንነታቸው እንዲጠበቅና የአመጋገብ ሥርዓታቸው እንዲስተካከል ለወላጆችና አሳዳጊዎች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡
የቀዳማዊ ልጀነት ልማት ፕሮግራም የድጋፍና የክትትል ባለሙያ አለም ወልዴ በበኩሏ በፕሮግራሙ ወላጆችን በመደገፍ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁማለች፡፡
የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ እንደገለጹት፤ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ልጆች የተስተካከለ የእድገት ሁኔታ እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩ የህፃናትን የእድገት ሁኔታ እያሻሻለ መምጣቱን ተናግረው፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር በዘርፉ ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡