የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ዘመን ተሻጋሪ የልማት አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ዘመን ተሻጋሪ የልማት አጀንዳ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሰራተኞች ማህበር አባላት ገለጹ።   

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰራተኞች ማህበር አባላት ጋር በመሆን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አካሂዷል።    


 

የችግኝ ተከላው በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቤላ 18 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው የተከናወነው።   

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰራተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ኑሁ ቺያም እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ  በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።   

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመከላከል ችግኞችን መትከል ሁነኛ መንገድ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ያመጣቸው ውጤቶች በአርዓያነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

አዲስ አበባ አረንጓዴ እና ጽዱ ከተማ መሆኗን አድንቀው፥ ይህም ሌሎች ሀገራትን የበለጠ እንደሚያነሳሳ ገልጸዋል።         

የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝብን በስፋት በማነቃነቅ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ እንዲሳተፉ ማድረጉ የሚደነቅና ለሌሎች ሀገራትም አብነት የሚሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።  


  

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰራተኞች ማህበር አባል ወጣት ጆን ማጎክ በበኩሉ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉን ገልጾ ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረበት ጠቁሟል።        

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ ቁርጠኛ መሆኗን የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ውጤት ዋነኛ ማሳያ መሆኑንም ተናግሯል።  


     

ሌላዋ የማህበሩ አባል ሞሮሲ ፑትሶዋ በበኩላቸው አረንጓዴ ዐሻራ በአህጉር  ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል  ለሚደረገው ጥረት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል።    

ኢትዮጵያ የዳበረ የአረንጓዴ ዐሻራ ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን በማንሳት፥ የአፍሪካ ሀገራት ውጤታማ የኢትዮጵያን ተሞክሮዎች በሀገራቸው በመተግበር ለትውልድ የሚተላለፍ ዐሻራን ማኖር እንዳለባቸው አመልክተዋል።  


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ በበኩላቸው፤ የዛሬው ችግኝ ተከላ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ የሰጠችውን ትኩረት በተጨባጭ ለማሳየት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።     

ይህም የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት በኩል ሚናው የላቀ መሆኑንም አስረድተዋል።  
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ በአህጉር ደረጃ አጀንዳ እንዲሆን የተጀመረው ጥረት ግቡን እንዲመታ በማድረግ ረገድ የዛሬው መርኃ ግብር ከፍ ያለ አበርክቶ እንደሚኖረውም አብራርተዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም