ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ በአህጉራዊ መድረክ ቅድመ ማጣሪያ የሚገጥሟቸውን ክለቦች አውቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ በአህጉራዊ መድረክ ቅድመ ማጣሪያ የሚገጥሟቸውን ክለቦች አውቀዋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/ 2017(ኢዜአ)፦ የ2025/26 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ በታንዛንያ ዳሬሰላም ተካሄዷል።
የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ በመጀመሪያ ቅድመ ማጣሪያ ዙር ከዛንዚባሩ ምላንዴጌ ኤፍሲ ጋር ይጫወታል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታ ከመስከረም 9 እስከ 11 ቀን 2018 ዓ.ም፣ የመልስ ጨዋታው ደግሞ ከመስከረም 16 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም መካከል ባለው ጊዜ እንደሚካሄድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።
ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲሳተፍ የመጀመሪያው ሲሆን ተጋጣሚው ምላንዴጌ ኤፍሲ በውድድሩ ላይ ሁለተኛ ተሳትፎውን ያደርጋል።
ምላንዴጌ ኤፍሲ የወቅቱ የዛንዚባር ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሲሆን በአጠቃላይ የሊጉን ዋንጫ ስምንት ጊዜ አንስቷል።
መድን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በቀጣዩ ዙር ከሩዋንዳው ኤፒአር እና ከግብጹ ፒራሚድ ኤፍሲ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
በተያያዘም በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ወላይታ ድቻ በመጀመሪያ ዙር ቅድመ ማጣሪያ ከሊቢያ ክለብ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
የቡድኖቹ ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታ ከመስከረም 9 እስከ 11 ቀን 2018 ዓ.ም፣ የመልስ ጨዋታው ደግሞ ከመስከረም 16 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም መካከል ባለው ጊዜ ይካሄዳል።
የሊቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ውድድር እስከ አሁን ባለመጠናቀቁ ምክንያት በውድድሩ ላይ የሚሳተፈውን ክለብ ያላሳወቀ ሲሆን ካፍ ተሳታፊው ክለብ እስኪታወቅ ድረስ “Libya 2” በሚል እጣውን አውጥቷል።
ወላይታ ድቻ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሲሳተፍ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ክለብ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ከግብጹ ፒራሚድስ ኤፍሲ ጋር ይጫወታል።
በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ 62 እንዲሁም በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ 52 ክለቦች ይሳተፋሉ።