የሕዳሴው ግድብ በአብሮነት ስንሰራ ግዙፍ ፕሮጀክትን ጀምረን መጨረስ እንደምንችል ያሳየንበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ በአብሮነት ስንሰራ ግዙፍ ፕሮጀክትን ጀምረን መጨረስ እንደምንችል ያሳየንበት ነው
ወልቂጤ/ሚዛን አማን ፤ነሐሴ 3/2017 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአብሮነት ከሰራን ግዙፍ ፕሮጀክትን ማሳካት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ሲሉ የወልቂጤና የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ ።
ነዋሪዎቹ ለግድቡ ግንባታና ሌሎች የልማት ስራዎች ሲያደርጉት የነበረውን እገዛ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የወልቂጤና የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች የኢትዮጵያዊያን የጋራ የትብብር ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአይቻልም መንፈስን በመስበር እንደሚቻል ያሳየንበት ነው ብለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ገነት ደምስስ እንዳሉት የሕዳሴው ግድብ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ ሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴን ያፋጥናል።
ግድቡ ልዩነትን ትተን በጋራ ከቆምን በራስ አቅም ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ያሉት ወይዘሮ ገነት፣ የዛሬው ትውልድ አይቻልም የተባለውን ግድብ እውን በማድረግ የራሱን ታሪክ አስቀምጧል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የበኩላቸውን ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር በቀጣይም መተባበርና በአንድነት መቆም ከተቻለ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክትን ጀምሮ መጨረስ እንደሚቻል ትምህርት የተገኘበት እንደሆነም አመልክተዋል።
"በእዚህ የልማት ውጤት ሳናበቃ ተጨማሪ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ትውልድ ተሻጋሪ ስራ መስራት አለብን" ሲሉም ገልጸዋል ።
"ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም ከፍ ያደረገና ጫናዎች ወደድል ለመቀየር ያስቻለ የስኬት ፕሮጀክታችን ነው" ያሉት ሌላው የከተማው ነዋሪ ደግሞ አቶ ጀማል አህመድ ናቸው።
ግድቡ የተፈጥሮ ሀብትን በራስ አቅም አልምቶ ለኢኮኖሚ ምንጭ መዋል እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ጠቁመው፣ ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት፣ በ8100 አጭር መልዕክት ገንዘብ በመላክና የአካባቢያቸውን ነዋሪዎች በማስተባባር ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ አቶ ገበየሁ ረጋሳ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህዝቦች አንድነት ጎልቶ የታየበት ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።
ግድቡ በአብሮነትና በአንድነት ከቆምን እንደምንችል ለመጪው ትውልድ እና ለዓለም ህዝብ ያሳየንበት የአብሮነት ውጤታችን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያዊያን ጠንካራ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የአይቻልም መንፈስን በማሸነፍ ግድቡ ወደመጠናቅቅ መድረሱ ለሀገር የልማት ጉዞ መፋጠን የራሱን ሚና እንደሚጫወት ገልጸው፣ በቀጣይም ትላልቅ ሀገራዊ የልማት ስራዎችን በጋራ የማሳካቱ ተግባር መቀጠል አለበት ብለዋል።
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው አቶ ተሰማ አሰፋ ግድቡ ከዓመታት በፊት ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበት እንደነበር አስታውሰው፣ የነበሩ ጫናዎችን በመቋቋም ዛሬ ለመመረቅ መጠጋቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ለግድቡ ግንባታ በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ ደማቅ አሻራቸውን አሳርፈዋል ያሉት ነዋሪው፣ በቀጣይም ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ልማትን ለማፋጠን የተጀመሩ ስራዎችን መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት የበኩላቸውን እገዛ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፣ በቀጣይም በሀገርና በአካባቢያቸው የልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።