ኮሚሽኑ የተፋሰሱ ሀገራት በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን የጥርጣሬ ዕይታ ወደ ትብብርና የጋራ ልማት እንዲቀየር ሚናው ከፍተኛ ነው - የዘርፉ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ የተፋሰሱ ሀገራት በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን የጥርጣሬ ዕይታ ወደ ትብብርና የጋራ ልማት እንዲቀየር ሚናው ከፍተኛ ነው - የዘርፉ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2017(ኢዜአ)፦ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን የተፋሰሱ ሀገራት በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን የጥርጣሬ ዕይታ ወደ ትብብርና የጋራ ልማት እንዲቀየር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ።
የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤትን በኡጋንዳ ኢንቴቤ በተቋም ደረጃ ማቋቋም የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል።
በ45 አንቀጾች የተዋቀረው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት ዋና ዋና መርሆች መካከል ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም፣ በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ እንዲሁም በፈቃደኝነት መተባበር የሚሉት ይጠቀሳሉ።
ለዓመታት ከቆየ ድርድር በኋላ ግንቦት 2002ዓ.ም በኡጋንዳ ኢንቴቤ ለፊርማ የቀረበው ሥምምነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገሮች ፈርመው በህግ አውጪ አካል አጸድቀውታል።
የሥምምነት ሰነዱን ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳና ደቡብ ሱዳን ፈርመው ማጽደቃቸውን ተከትሎ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ተፈጻሚነት መግባቱም ይታወሳል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዘርፉ ባለሙያዎች ስምምነቱ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን መቋቋሙን ያብራራሉ።
ኮሚሽኑ በሥምምነት ማዕቀፉ ውስጥ የተደነገጉ መርሆዎች፣ መብትና ግዴታዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የውሃ ሃብት አስተዳደር፣ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞችና የሃይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪው ፈቅ አሕመድ ነጋሽ፤ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ቆይቶ ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውሰዋል።
ይሁንና ኮሚሽኑን በተቋም ደረጃ ከማቋቋም ጀምሮ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ያነሳሉ።
የዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ባለሙያው ከበደ ገርባ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኮሚሽኑ በሀገር መሪዎች ኮንፍረንስ፣ የውሃ ሚኒስትሮች ካውንስል፣ በአማካሪ ባለሙያዎች ቡድንና በዋና ፀሃፊ መዋቀሩን ይናገራሉ።
በዚህ መሰረት በየደረጃው የተጀመሩ ውይይቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ በኡጋንዳ ኢንቴቤ ጽሕፈት ቤት የመክፈትና በሰው ሃይል የማሟላት ዝግጅቶች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ፣ ኮሚሽኑ በዋናነት በትብብር ማዕቀፍ ሥምምነቱ ላይ የተደነገጉ መርሆዎች፤ መብቶችና ግዴታዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ያስተባብራል።
የናይል ውሃን ለመጠቀም፣ ለማልማትና ለማስተዳደር ለተፋሰሱ አባል ሀገሮች ተቋማዊ የትብብር ማዕቀፍ በመሆን እንደሚያገለግል ነው ያብራሩት።
እኤአ በ2015 በሱዳን ካርቱም የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና ሱዳን መሪዎች የፈረሙት የመርሆ ስምምነት "Declaration of Principles"(DOP) በጋራ መስራትን በማበረታታት እንደ አንድ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት የቅኝ ግዛት ውሎችን ውድቅ የሚያደርግና በተፋሰሱ ሀገራት አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት ብቸኛ የሕግ ማዕቀፍ መሆኑንም ተናግረዋል።
የስምምነት ሰነዱ ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘት በተፋሰሱ ሀገራት የአባይ ወንዝ የግጭትና የጥርጣሬ ምክንያት ሳይሆን የትብብርና በጋራ የመልማት አዲስ እይታ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑም የተፋሰሱ አባል ሀገራት አለመግባባቶች ሲያጋጥማቸው እልባት የሚሰጥና መብትና ግዴታቸውን እንዲያከብሩ የሚያስገድድ መሆኑንም እንዲሁ።
ባለሞያዎቹ ኢትዮጵያ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት እውን እንዲሆን የምታበረክተውን የመሪነት ሚና አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል።
ኮሚሽኑ ጠንካራና በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀምን እውን እንዲያደርግ ያልፈረሙ ቀሪ ሀገራትም ስምምነቱን እንዲፈርሙ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ባለሙያዎቹ አንስተዋል።