የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ወጥነትና ዘላቂ ማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ወጥነትና ዘላቂ ማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው - ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2017(ኢዜአ)፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ወጥነትና ዘላቂ ማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከዘመቻ በማላቀቅ ወጥነት ባለው አግባብ ለማከናወን ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡
ሚኒስቴሩ ብሔራዊ ረቂቅ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ አዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡን በሚኒስቴሩ ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስፋፊያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዐቢይ ኃ/መለኮት ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በዘላቂነት ለማከናወን ዘርፉን በፖሊሲ፣ በዕቅድ፣ በበጀትና በሰው ኃይል በማደራጀት ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በትምህርት ሥርዓቱ በማካተትም ተማሪዎች ባህል እንዲያደርጉት መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ማኅበራትን ማበራከትና ሕብረተሰቡም በንቃት እንዲሳተፍባቸው ዕድሎችን ማመቻቸት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለማኅበራዊ ለውጥ የጎላ ድርሻ እንዳለው የሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳዩ ጠቁመው ከዚህ ልምድ በመውሰድ በኢትየጵያ በስፋት መከናወን እንዳለበት ታምኖበት በትጋት እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም አምራችም ሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከዘመቻ በማላቀቅ ወጥነት ባለው አግባብ በእቅዳቸው በማካተት የልማት ማሳለጫ ቁልፍ መሳሪያ አድርገው እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህን ተግባር ወጥና ቀጣይነት ያለው ማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ ረቂቅ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ አዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡንም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም የተለያዩ ስታንዳርዶችና የአሠራር ሥርዓቶች መዘጋጀታቸውን፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፌደራል እስከ ቀበሌ መዋቅር ኖሮት እንዲሠራ እየተደረገ መሆኑን፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሥተዳደርን ማከናወንን ጨምሮ አገልግሎቱ እንዲሰርጽ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ዘላቂ በማድረግ ባህል እንዲሆን በሚኒስቴሩ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡