ደብረ ማርቆስ ከተማን ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹና ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ ነሀሴ 2/2017(ኢዜአ)፡-የደብረ ማርቆስ ከተማን ጽዳትና ውበት በማጠናከር ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹና ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። 

በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር "የጽዱ ኢትዮጵያ" መርሃ ግብር አካል የሆነ የጽዳት ዘመቻ ዛሬ ተጀምሯል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ የጽዳት ዘመቻውን ሲያስጀምሩ እንደገለጹት፣ የሰላምና ጽዳት ሥራዎች ለሰው ልጅ ህይወት ወሳኝ በመሆናቸው በከተማዋ በትኩረት ይተገበራሉ። 

የጽዱ ኢትዮጵያን መርህ በከተማዋ በመተግበር ጽዳትን ከራስ ጀምሮ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በአካባቢ ለማስፋት የሚያስችል ዘመቻ ዛሬ መጀመሩንም ተናግረዋል።

የጽዳት ሥራውን አጠናክሮ በማስቀጠል ከተማዋን ጽዳትና ውበት በማጠናከር ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቸርነት አለማየሁ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የከተማዋን ጽዳት በመጠበቅ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።


 

የጽዳት ሥራው ማህበረሰቡ ግቢውንና አካባቢውን ማጽዳት ባህሉ እንዲያደርግ ያለመ መሆኑን ገልጸው፣ "በከተማዋ የጽዱ ኢትዮጵያ" መርህን ለማሳካት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ቀጣይነት ያለው ሥራ ይሰራል ብለዋል።

የከተማዋን ውበት የሚያሳድጉ መሰረተ ልማቶች ላይ ቆሻሻ የሚጥሉ አካላት እንዳሉ የገለጹት አቶ ቸርነት፣ በጽዱ ኢትዮጵያ መርሀግብር ዛሬ የተጀመረው የጽዳት ዘመቻ ይሄን ችግር ይፈታል ብለዋል።


 

ከጽዳት ዘመቻው ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ትግስት ምህረት "የጸዳች ሀገርና ከተማ እንድትኖረን አካባቢዬን በማጽዳት የማደርገውን አስተዋጾ አጠናክራለሁ" ብላለች።

የጽዱ ኢትዮጵያን መርህ መነሻ በማድረግ ዛሬ በተካሄደ የጽዳት ዘመቻ በከተማ አስተዳደሩ ያሉ የመንግስት ሠራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም