ቀጥታ፡

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ሀገራዊ ግብን የሚያሳኩ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2017(ኢዜአ)፦ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ሀገራዊ ግብን የሚያሳኩ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

ኮሚሽኑ "ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም" እሳቤን በሚመለከት ከማዕከል እና ክልል ተጠሪ ተቋማት ለተወጣጡ የዘርፉ ሙያተኞች በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለፁት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ ተስማሚና ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ ያላት አገር ናት።

ያላትን እምቅ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ ለበርካታ ዓመታት ስሟ ከተረጂነት ጋር ሲነሳ መቆየቱን አውስተዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን መንግስት ተረጂነትን ለማስቀረትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ በርካታ የልማት ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ "ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም" በሚል እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የተረጂነት አስተሳሰብንና ተግባርን የሚያስቀሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በምግብ ሉዓላዊነት ዙሪያ ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ፣ የሀገራትን ልምድና ተሞክሮን የቀመረ አሰራርን እያጠናከሩ መቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል።

በመሆኑም ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ሀገራዊ ግብን ለማሳካት የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ተረጂነትን መቀልበስ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው ብለዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ስልጠና በየአካባቢው ያሉ ሀብቶችን አልምቶ መጠቀምና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን ብቁ ቁመና መገንባት የሚቻልባቸውን አማራጮች ለማየት እድል የሚፈጥር ስለመሆኑም ተገልጿል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም