የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት መሰረት የሚሆን ስኬት አስመዝግቧል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት መሰረት የሚሆን ስኬት አስመዝግቧል - ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2017(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት መሰረት የሚሆን ስኬት ማስመዝገቡን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት የሚያስተዋውቅ ፊውቸር ቴክ-2025 ኤክስፖ በመጪው ኅዳር ወር በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አይሲቲ ፓርክ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ ፊቸር ቴክ-2025 ኤክስፖ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና የ5 ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ተግባራትን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል።
በዚሁ ጊዜ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉቀን ቀሬ፥ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።
ከመጪው ኅዳር 19 እስከ 21/2018 ዓ.ም ድረስ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሄደው ፊቸር ቴክ-2025 ኤክስፖ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስኬቶችን ለማስቀጠል ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
በኤክስፖው ላይ የቴክኖሎጂ ክህሎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ የግልና የመንግስት ኩባንያዎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያውያን በዲጂታል የኢኮኖሚ ሥርዓት ግንባታ ላይ እንዲሳተፉም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ ያቀረቡት።
የኢትዮጵያ የአይሲቲ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሔኖክ አሕመድ፥ በፊቸር ቴክኖሎጂ ኤክስፖ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተመዘገቡ ስኬቶች ይቀርባሉ ብለዋል።
በስትራቴጂው መነሻነት በመንግስትና በግል ዘርፍ የቴክኖሎጂ ልማት ምርትና አገልግሎቶች ለእይታ የሚቀርቡበት መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ኤክስፖው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለማስተዋወቅ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ነው ጨምረው የተናገሩት።
ኤክስፖው በአይሲቲ ፓርክ የተገነቡና በግንባታ ሂደት የሚገኙ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ስራዎችን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ(ዶ/ር)፥ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሀገርን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጡ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በዲጂታል ክህሎት ልማት፣ ዲጂታል ፋይናንስ፣ በዲጂታል መታወቂያ፣ በመንግስት አገልግሎቶች፣ የኦንላይን ንግድ ሥርዓትና በ5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ተጨባጭ ስኬት መመዝገብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ የተመዘገቡ ስኬቶችን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የስታርታፕ አዋጅን ጨምሮ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት መሰረት የሚሆን ስኬት ማስመዝገቡን አስታውቀዋል።
የኖቫል ልማትና ትብብር የምርምር ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሬድዋን አብዲ፥ ኤክስፖው የመንግስትና የግል ቴክኖሎጂ ልማት አጋርነትን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
በኤክስፖ 1ሺህ የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን በማሳተፍ በኢትዮጵያ የሚኖራቸውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማስፋት በኢንቨስትመንትና ዲፕሎማሲ፣ በክህሎትና ፈጠራ፣ በፖሊሲና ልማት አጋርነት ላይ ትኩረት ማድረጉን አስታውቀዋል።
በኤክስፖው የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የቴክኖሎጂ የልማት አጋሮችና አልሚ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።