የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ከታቀደለት ጊዜ ፈጥኖ በሁሉም መስክ እንዲሳካ በበለጠ ትጋት እንሰራለን − የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ከታቀደለት ጊዜ ፈጥኖ በሁሉም መስክ እንዲሳካ በበለጠ ትጋት እንሰራለን − የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ከታቀደለት ጊዜ ፈጥኖ በሁሉም መስክ ለማሳካት ከወትሮው በበለጠ ትጋት እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 02 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
በዚህ መደበኛ ስብሰባ በዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ ቀጣናዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መወያየቱን ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ብልጽግና በሁሉም መስክ እንዲሳካ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት እንደሚሰራ ያስታወቀው ምክር ቤቱ፤ ለብልጽግና ጉዞ እንቅፋት የሚሆኑትን አስተሳሰቦች፣ ባህሎች፣ ልማዶች፣ ሰርጎ ገቦች እና ባንዳዎች ተግቶ እንደሚያጠራ አስታውቋል።
ፓርቲው “መመከት፣ መትጋትና ማጥራት” በሚል መርህ ቀጣዩን ተግባር ለማከናወን መወሰኑን ገልጾ፤ ለሚገነባው ሀገር፣ ለሚቆምለት ዓላማ እና ሕልም እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅም በትጋት እንደሚታገል አመልክቷል።
ማልማት፣ መገንባት እና ማጽናት ከማጥፋት፣ ከማደናቀፍ እና ከማፍረስ በላይ ዐቅምና ትጋት እንደሚጠይቅ ያመለከተው መግለጫው፤ ጠላቶች ይህን ለማጥፋት፣ ለማፍረስና ለማሰናከል እንደሚፈልጉ አንስቷል።
ተግዳሮቶችን ሁሉ ተቋቁሞ ብሄራዊ ራዕይን ለማሳካት የሚችል ብሄራዊ አቅም መገንባቱን እንደሚቀጥል በመግለጫው ያረጋገጠው የፓርቲው ምክር ቤት፤ ከሁሉም በላይ ሰላማዊ የፖለቲካ ዕድሎችን አሟጦ የሚጠቀም መሆኑንም ገልጿል።
ባለፉት ዓመታት ተግዳሮቶች ቢበረቱም በሁሉም መስክ ድል ከማስመዝገብ ባለፈ በሶስት ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን አብራርቷል።
ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በተግዳሮቶች ሳይበገሩ ማንሰራራታቸውን ያመለከተው መግለጫው፤ ይህም ውስጣዊ ተጋላጭነታችንን አጥብቦ፣ ባንዳዎችን ቦታ አሳጥቷል ሲል ገልጿል።
በዓባይ ላይ ተገቢውንና ሕጋዊውን ተግባር በማከናወን በቀጣናው ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመናን ለውጠናል ያለው ምክር ቤቱ፤ የባሕር በር የማግኘት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብትም ዓለም አቀፍ አጀንዳ መደረጉን አስታውቋል።
በዚህም በቀይ ባሕር የነበረንን ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና ለመመለስ ከአንድ ምዕራፍ በላይ ተራምደናል ነው ያለው በመግለጫው።
በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ለውስጣዊ ተጋላጭነት መነሻ መሆናቸው ቀርቶ ወደ ብሄራዊ አቅምነት መቀየራቸውን አብራርቷል።
በህብረ ብሄራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ መንገድ መቀየሱን በመግለጫው ጠቁሞ፤ በአንድ በኩል በተጀመሩት ተቋማዊ ሪፎርሞችና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሀገሪቱ ውስጣዊ አቅም መጠናከሩን በሌላ በኩል የጂኦ ፖለቲካዊ ቅኝትን በሚገባ በመገንዘብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ማስከበሩንም አመልክቷል።
የምክር ቤቱ አባላት በቃልም በተግባርም ዝግጁ በመሆን በቆራጥነት ውጤታማ እንደሚሆኑ በመጥቀስ፤ አሁን ከሚጠበቅባቸው በላይ ለማከናወን ቆርጠው መነሳታቸውን መግለጫው አስረድቷል።
ግጭትን ሊያስቀሩ የሚችሉ ሰላማዊ አማራጮችን በሁሉም አቅጣጫ ለመሞከርና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለሚወስኑ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ምክር ቤቱ ገልጿል።
የሰላምን አማራጭ ባለመቀበል በሕዝብና በሀገር ንብረት ላይ ችግር ለመፍጠር በሚነሡ ኃይሎች ላይ በተጠናከረ መንገድ ሕግ የማስከበር ተግባር እንደሚከናወን አብራርቷል።
በየደረጃው የሚነሡ የሕዝብ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በኢትዮጵያ ዐቅም ልክ በየደረጃው ለመመለስ የወሰነው ምክር ቤቱ፤ ተገቢውንና እውነተኛውን መረጃ ለሕዝብ በየጊዜው ለመስጠትና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጋለጥ መወሰኑን አመልክቷል።
በየተቋማቱ ተመድበው የዲሲፕሊን ጉድለት፣ ሙስናና የአስተዳደር በደል የሚያደርሱ የሥራ መሪዎችንና አገልጋዮችን እንደሚታገልም አረጋግጧል።
በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የበለጠ ስኬታማ በማድረግ፤ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን ለውጤት በማብቃት፤ የሕዝብን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ የከተማና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚተጉ አመልክቷል።
በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በሁሉም መንገድ ለማስከበር፤ ከመግባባት ላይ መደረሱንም ገልጿል።