ለቡና ምርት እና ጥራት የተሰጠው ትኩረት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያሳደገው ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለቡና ምርት እና ጥራት የተሰጠው ትኩረት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያሳደገው ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ነሐሴ 2/2017(ኢዜአ)፦ለቡና ምርትና ጥራት ትኩረት መሰጠቱ ዘርፉ እንዲያንሰራራ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው እያደገ እንዲመጣ ማድረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ አባላትና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት መንግስት ለቡና ምርትና ጥራት የሰጠው ትኩረት ዘርፉ እንዲያንሰራራ አድርጓል።
ይህም ከዘርፉ የሚጠበቀው ገቢ እያደገ እንዲመጣና አምራቹና ነጋዴው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተያዘው በጀትም ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።
ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በተለይ ቡና አምራቾችና የማህበሩ አባላት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ግንዛቤያቸውን ለማሳደግ ታስቦ በየአካባቢው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
በቡና ንግድ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ የህገ ወጥነት ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ባለድርሻዎችን በማሳተፍ በሰራው ሥራ ውጤት መገኘቱንና ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራም አመልክተዋል።
መንግስት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ከቀጠለ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም ሁሴን (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የቡና ነጋዴዎች በአንድ ማህበር መደራጀታቸው ነጋዴውን ከገዢ ጋር በማገናኘት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን ቡና ማህበር ሰብሳቢ አቶ ከበደ ለማ ናቸው።
ከብሔራዊ ማህበሩ ጋር በቅንጅት መስራታቸው ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው፣ በ2018 በጀት ዓመት የወላይታ ቡናን ጥራት በማሳደግ 30 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል።
በባስኬቶ ዞን የላስካ ዙሪያ ወረዳ የሻይ፣ ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መነጎድ በበኩላቸው በዞኑ የቡና ማህበር መመስረቱ በዘርፉ በህገወጥ ተግባር የተሰማሩትን ከመስመር እንደሚያስወጣ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከቡና ንግድ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ አምራቹን፣ ነጋዴውንና መንግስትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በማህበር ተደራጅቶ መንቀሳቀስ የቡና አቅርቦትና አቅምን ለማሳደግ ካለው ፋይዳ በተጨማሪ በዘርፉ በህገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በጋራ ለመከላከል ወሳኝ መሆኑንም አቶ ኤርሚያስ አስረድተዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር አመራሮች እና አባላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።