ቀጥታ፡

ፊውቸር ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በመጪው ኅዳር ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 2 /2017(ኢዜአ)፦ፊውቸር ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በመጪው ኅዳር ወር በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አይሲቲ ፓርክ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን፣ ፊውቸር ቴክኖሎጂ ኤክስፖ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና የ5 ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ተግባራትን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉቀን ቀሬ፣ የኢትዮጵያ የአይሲቲ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሔኖክ አሕመድ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) እና የኖቫል ልማትና ትብብር የምርምር ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሬድዋን መግለጫውን በጋራ ሰጥተዋል። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉቀን ቀሬ፥በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ማሳደግ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል ብለዋል። 

ከመጪው ኅዳር 19 እስከ 21/2018 ዓ.ም ድረስ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሄደው ፊውቸር ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025  የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬቶችን ለማስቀጠል ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል። 

በኤክስፖው ላይ የቴክኖሎጂ ክህሎት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን፣ የግልና የመንግስት ኩባንያዎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

ኢትዮጵያዊያን በዲጂታል የኢኮኖሚ ሥርዓት ግንባታ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸውም አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ የአይሲቲ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሔኖክ አሕመድ፥ ፊውቸር ቴክኖሎጂ ኤክስፖ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተመዘገቡ ስኬቶች እንደሚቀርቡበት ጠቁመዋል። 

በስትራቴጂው መነሻነት በመንግስትና በግል ዘርፍ የቴክኖሎጂ ልማት ምርትና አገልግሎቶች ለእይታ እንደሚቀርቡ ገልጸው፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለማስተዋወቅም ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል። 

ኤክስፖው በአይሲቲ ፓርክ የተገነቡና በግንባታ ሂደት የሚገኙ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ልማት ስራዎችን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን አስታውቀዋል። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር)፥ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሀገርን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጡ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በዲጂታል ክህሎት ልማት፣ ዲጂታል ፋይናንስ፣ በዲጂታል መታወቂያ፣ በመንግስት አገልግሎት፣ የኦንላይን ንግድ ሥርዓትና በ5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ተጨባጭ ስኬት ማስመዝገብ እንደተቻለ ገልጸዋል። 

በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ የተመዘገቡ ስኬቶችን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የስታርት አፕ አዋጅን ጨምሮ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የኖቫል ልማትና ትብብር የምርምር ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሬድዋን አብዲ፥ ኤክስፖው የመንግስትና የግል ቴክኖሎጂ ልማት አጋርነትን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም