አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ ምቹ ሀገርን የመገንባት ትልቅ ተነሳሽነት ነው- የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ ለትውልድ ምቹ ሀገርን የመገንባት ትልቅ ተነሳሽነት በመሆኑ ተሳትፏችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።

በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በሸገር ከተማ መነ አብቹ ክፍለ ከተማ የችግኝ ተከላ መርሃግብር አካሂደዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ሰለሞን ታፈሰ በዚሁ ወቅት፥ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለትውልዱ የተሻለችና ምቹ ሀገርን የመገንባት አጀንዳ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራርና አባላትን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሰለፍ ይገባል ያሉት ሰብሳቢው፥ ለአብነትም በልማት፣ በሰላም እና የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሰለፍ እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት።

መንግስት የተፎካካሪ ፓርቲዎች በዚህ  ሂደት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ገልጸዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ኃላፊ ሞገስ ኢደኤ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የማይገድበው የጋራ ሀገራዊ አጀንዳ ነው ብለዋል።


 

የፖለቲካ ፓርቲዎች አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በሀገራዊ ጉዳዮች ተቀራርበው መስራታቸው ለሀገር እድገትና ለዴሞክራሲ ባህል መዳበር አጋዥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኦሮሚያ ክልል የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ፀሐፊ ታሪኩ ድንበሩ፥ አረንጓዴ አሻራ ነገን የተሻለ ለማድረግ ትልቅ ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸዋል።


 

የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነፃነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሮበሌ ታደሰ፥ አረንጓዴ አሻራ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የሁሉም ጉዳይ በመሆኑ ተሳትፏችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።


 

አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ አባል ኤርሚያስ ተገኔ  ናቸው።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም