ቀጥታ፡

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን ከፍተኛ ሚና አላቸው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2017(ኢዜአ)፦የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተረጂነትን  በማስቀረት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ። 

ኮሚሽኑ "ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም" እሳቤን በሚመለከት ከማዕከል እና ከክልል ተጠሪ ተቋማት ለተወጣጡ የዘርፉ ሙያተኞች በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።


 

ስልጠናውን በሚመለከት የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) እንደገለፁት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ ተስማሚና ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ ያላት አገር ናት።

ያላትን እምቅ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ ለበርካታ ዓመታት ስሟ ከተረጂነት ጋር ሲነሳ መቆየቱን አውስተዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን መንግስት ተረጂነትን ለማስቀረትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ በርካታ የልማት ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ "ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም" በሚል እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የተረጂነት አስተሳሰብንና ተግባርን የሚያስቀሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።


 

የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አሰራሩን በአግባቡ በመረዳት ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ስልጠና በየአካባቢው ያሉ ሀብቶችን አልምቶ መጠቀምና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን ብቁ ቁመና መገንባት የሚቻልባቸውን አማራጮች ለማየት እድል የሚፈጥር ስለመሆኑም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም