ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማልማት ለትውልድ ግንባታ እንዲውሉ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማልማት ለትውልድ ግንባታ እንዲውሉ እየሰራ ነው

ወልቂጤ፤ነሐሴ 2 /2017(ኢዜአ)፦ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማልማት ለትውልድ ግንባታ እንዲውሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ የመማር ማስተማር ስራ ባሻገር በአካባቢው ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት፣ በሃገረሰባዊ መድሃኒት አመራረት፣ በሰላም ማፅኛ እሴቶች፣ በጀፎረ እና በቋንቋ ልማት ላይ እየሰራ ይገኛል።
እነዚህን ሃገር በቀል እውቀቶች በጥናትና ምርምር ሥራዎች ታግዞ በማልማት ለትውልድ እንዲተላለፉ እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር መለሰ እጥፉ እንዳሉት ነባር ሃገረሰባዊ እሴቶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ዩኒቨርሲቲው በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየሰራ ነው።
ለዚህም የማህበረሰቡን እሴቶች በማጥናትና በማስተዋወቅ ለሀገር እድገትና ለትውልድ ግንባታ ለማዋል የቋንቋ፣ የባህል እና የሃገር በቀል እውቀት ልማት ማዕከል በአዲስ መልክ ማቋቋሙን ተናግረዋል።
ለአብነት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በጉራጊኛ ቋንቋ ማስተማሪያ መፅሀፍት፣ በፊደላት ቀረጻና መተግበሪያ አፕልኬሽኖችን እንዲሁም በመማር ማስተማር ስነ ዘዴ ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቅስዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቋንቋ፣ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን በበኩላቸው የቋንቋ መምህራን የማህበረሰቡን እሴቶች ጠብቀው ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው አጎራባች ያሉ የጉራጌ፣ የየም፣ የቀቤና እና የኦሮሞ ባህልና ሀገር በቀል እውቀቶችን ለማልማት እና ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
የጉራጊኛ ቋንቋ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ትምህርት እየተሰጠበት መሆኑን ጠቁመው፣ ዩኒቨርሲቲው ቋንቋውን የሚያስተምሩ መምህራንን አቅም የማጎልበት ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም ማህበረሰባዊ እሴቶችን ለማጉላት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማጠናከር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ የመምህራን ልማት ባለሙያ አቶ መሃመድ አማን እንዳሉት ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መመቻቸቱ በቀላሉ እውቀት እንዲጨብጡ ይረዳቸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በጉራጊኛ ቋንቋ ላይ ጥናት ከማድረግ በተጨማሪ የመምህራን አቅም ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።