የባህር በር የማግኘት መብትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነትን ማጠናከር ይገባል - አቶ አብዱልበር ሸምሱ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 1 /2017(ኢዜአ)፦ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር መተላለፊያ የማግኘት መብት የሚያረጋግጡ ዓለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎችን ተፈጻሚነት ማጠናከር ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ ገለጹ።

ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በማደግ ላይ የሚገኙ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ኮንፍረንስ በተርኪሚኒስታን መካሄዱን ቀጥሏል።


 

ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን ዘላቂ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ትስስርን ማጠናከር እና ያልተገደበ የትራንዚት አገልግሎት ስርዓትን የተመለከተ ውይይት ዛሬ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ በውይይቱ ላይ በሰጡት ሀሳብ ዘላቂ መሰረተ ልማት እና ውጤታማ የትራንዚት ስርዓቶች የኢትዮጵያ የልማት ስትራቴጂ አበይት የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ መንገድ፣ የባቡር መስመር ፣ ደረቅ ወደቦች እና የሎጅስቲክስ ማዕከላትን ጨምሮ በትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሷን አመልክተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የ750 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ለማሳያነት አቅርበዋል።

አረንጓዴው ኮሪደር ከታዳሽ ኃይል የሚመነጭ ኤሌክትሪክ በመጠቀም ብክለት እና የትራንዚት ጊዜን በመቀነስ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

ስምንት ደረቅ ወደቦች መቋቋማቸውን ጠቅሰው፥ ወደብ ላይ ያለ መጨናነቅን ከማቃለል፣ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ማጠናከር እና የጉምሩክ አገልግሎትን ከማሳለጥ አኳያ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ቀጣናዊ የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስር ከማጠናከር አኳያም ኢትዮጵያ ኮሪደርን መሰረት ያደረገ የትስስር ሞዴል እየተገበረች መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ፣ የአዲስ አበባ እና ናይሮቢ እንዲሁም ኢትዮጵያ፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርት የሚያስተሳስረው የ"ላፕሴት ፕሮጀክት" ጨምሮ ስትራቴጂካዊ የመሰረተ ልማት ኮሪደሮች መኖራቸውን ነው ያነሱት።

የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የጉምሩክ አገልግሎት፣ የዳታ ትስስር እና ሌሎች ዲጂታል ስርዓቶች በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ገቢራዊ እንደሆኑም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ስትራቴጂ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ጋር ሙሉ ለሙሉ የተጣጣመ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ይህም የገበያ ተደራሽነትን እንደሚያረጋግጥ አብራርተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ከባህር በር የማግኘት መብት እና ህጋዊ ማዕቀፎች አንጻር ባነሱት ሀሳብ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የተደነገጉ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር መተላለፊያ እና ትራንዚት የማግኘት መብት መጠበቅ ከፍተኛ አጽንኦት የምትሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።

በአዋዛ የድርጊት መርሃ ግብር (Awaza Programme of Action) በማደግ ላይ የሚገኙ የባህር በር የሌላቸው ሀገራትን ህጋዊ መብትን ማስከበር የሚቻልባቸው አማራጮች እንዲፈልግ የተቋቋመው የተመድ ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ አሰራሮች የዓለም አቀፍ የትራንዚት መብቶች ተፈጻሚነት አፈጻጸምን በጥልቀት ሊፈትሹ ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የባህር በር እና የትራንዚት መስመር ያላቸው ሀገራት የባህር በር የሌላቸውን ሀገራት መብቶችን ተፈጻሚ የሚያደርጉበትን መንገድ በህግ በተቀመጡ ኃላፊነቶች እና ማዕቀፎች አስገዳጅ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከቀጣናዊ ጉዳዮች አንጻር ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን በጋራ ያቋቋሙት የኮሪደር አስተዳደር ባለስልጣን በንግድ መስመሮች ላይ ግልጽነት፣ ውጤታማነት እና ፍትሃዊነትን የበለጠ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአንድ ማዕከል የድንበር አገልግሎት እና የጉምሩክ ህጎችን ወጥ ማድረግን ጨምሮ ፖሊሲዎችን በማሰናሰን ስኬታማ ስራዎች እያከናወነች ነው ብለዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታ እና ትስስርን እያፋጠነች እንደምትገኝም በማንሳት።

የቀጣናው እና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች የአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን የማሳካት እና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ የጋራ ራዕይ ስኬት በትብብር እንዲሰሩ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በማደግ ላይ የሚገኙ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ኮንፍረንስ ነገ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም