ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ የሆነ " ሸነል" የተሰኘ ተገጣጣሚ የግንባታ ቴክኖሎጂ በሙሉ አቅም ወደ ስራ ገባ

ባህርዳር፤ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፡- ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ የሆነ "ሸነል" የተሰኘን ተገጣጣሚ የግንባታ ቴክኖሎጂ በሙሉ አቅም ወደ ስራ ማስገባት መቻሉ ተገለጸ። 

በአማራ ክልል መንግስታዊ የልማት ድርጅት የሆነው ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች በተለያዩ ተቋማት ውል ወስደው እየገነቧቸው የሚገኙ የተለያዩ ህንጻዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታደሰ ግርማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ቴክኖሎጂው አለም አቀፍ የግንባታ መስፈርቶችን ያሟላ  ነው።

ቴክኖሎጂው ጀርመንና ጣሊያንን የመሳሰሉ ሀገራት  ቤት ለመስራት የሚጠቀሙበት መሆኑን አስረድተዋል።

በወጪ ደረጃም በአርማታና ብሎኬት ከሚገነቡ ህንጻዎች እስከ 40 በመቶ የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ ከ38 በመቶ በላይ በአጠረ ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

ቴክኖሎጂው በጥራቱና አዋጭነቱ በፌዴራል ደረጃ ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡ ይሄን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የመኖሪያ ቤቶችን በቀላል ወጪ መስራት እንደሚችል ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የነበሩ የግብአትና ሌሎች ችግሮችን ሙሉ በሙሉ በመፍታት በሙሉ አቅም ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን አስታውቀዋል።

በሙከራ ደረጃ የዘጠኝ ግለሰቦችን ቤት ገንብቶ ማስረከብ መቻሉን ጠቁመው፤   አሁን ላይ የአማራ ክልል ጤናና ግብርና ቢሮዎች እድሳትና አዳዲስ ህንጻዎች ግንባታን በቴክኖሎጂው እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በተጨማሪም የአማራ ክልል ልህቀት የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ቢሮን ገንብቶ ማስረከብ መቻሉን ገልጸው ፤ አሁን ላይ ቴክኖሎጂውን ፈልጎ ለሚመጣ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ  ስለሺ ሙሉነህ በበኩላቸው እንዳሉት፤  40 ሚሊዮን ብር በጨረታ የተጠየቀውን የማስፋፊያ ቢሮ ግንባታ በግማሽ በመቀነስ በቴክኖሎጂው ማስገንባት ተችሏል። 

ቴክኖሎጂው ወጪና ጊዜ ቆጣቢ ከመሆኑ በተጨማሪ ሰፊ የሰው ሃይል የማይጠይቅ፣ አገልግሎቱም ከብሎኬት ቤት የተሻለና ለአደጋ የማይጋለጥ መሆኑን  ገልጸዋል።


 

በክልሉ ልህቀት የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን የሪ-ኢኖቬሽን ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መስፍን ከበደ፤ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የቢሮ ግንባታ በአጠረ ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም