ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ፣ውጤታማና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠትና የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ የተሻለ ፈጽመዋል -የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፡-በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት የሕግ የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ የተሻለ መፈጸማቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2017 ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም በከፊል እንደሚዘጉም ተገልጿል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሙኒኬሽን  ጉዳዮች ዳይሬክተር (ተወካይ) ሰላም ዋርጋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል።

በበጀት ዓመቱ ለ187 ሺ 55 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ 190 ሺ 347 መዛግብት እልባት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ይህም ከእቅዱ በላይ መሳካቱን ያሳያል ብለዋል።

ከመዛግብት አፈጻጸም ባለፈም የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ሥርዓትን ከማጠናከር አኳያ የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል ነው ያሉት።

የዳኝነት ቅልጥፍናና የውሳኔ ጥራትን በማሳደግ፣ የዳኝነት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማገዝ እንዲሁም አካላዊ ተደራሽነትን በማስፋት አንጻር የተሻለ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ዳኞች የሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎት ክብደትና ውስብስብነትን ግምት ውስጥ በማስገባት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ መሰረት በየዓመቱ ለሁለት ወራት በቂ እረፍት እንዲያደርጉ የሚደረግ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ መሰረት ከዛሬ ነሀሴ 1ቀን 2017 ጀምሮ እስከ መስከረም 30/2018 ዓ.ም ድረስ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ይሆናሉ ነው ያሉት።

ይሁንና በባህሪያቸው አስቸኳይና ጊዜ የማይሰጡ በዜጎች መብትና በአገር ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አቤቱታዎች እንዲሁም ለውሳኔ የደረሱ መዛግብትን መርምሮ አገልግሎት የመስጠት ሥራው ይቀጥላል ብለዋል።

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች፣ ወጣት ጥፋተኞችን በሚመለከት የይግባኝ ጉዳዮች፣ ለወንጀል ምርመራ በቀረበ የጊዜ ቀጠሮና ዋስትናን የሚመለከቱ ጉዳዮችም በፍርድ ቤቶቹ የሚታዩ ይሆናል ብለዋል።

በፍትኃብሔር ጉዳዮች የቀለብና ተያያዥነት ያላቸው የቤተሰብ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታና ክርክሮች፣ የእግድና እንደ አስፈላጊነቱ አስቸኳይ መፍትሄ የሚፈልጉ አቤቱታዎችም በከፊል ዝግ በሚሆኑት ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ይሆናል  ነው ያሉት።

የሰበር አጣሪ ችሎቶች በመደበኛ ጊዜ የሚሰራውን አጣርቶ ውሳኔ የመስጠት ሥራ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በመደበኛ የዳኝነት አገልግሎት እንደሚሰጡም አንስተዋል።

በክረምት የእረፍት ጊዜ ውሳኔ ያገኙ መዛግብት ከጥቅምት 3 ቀን እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ለተከራካሪዎች በችሎት የሚገለጽ ሲሆን በእነዚህ ቀናት ባለጉዳዮች እንዲቀርቡና ውሳኔያቸውን እንዲሰሙ በስልክ ወይም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ይገለጻል ነው የተባለው።

በ2018 ዓ.ም ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ ውጤታማና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የህግ ማዕቀፎችና የአሰራር ክፍተቶችን በመለየት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የዳኝነት አገልግሎቱን የበለጠ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቱን የማጠናቀቅና ፍርድ ቤቶችን በኔትወርክ የማስተሳሰሩ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም