ደማችንን በመለገስ የወገኖቻችንን ህይወት መታደግ በመቻላችን ኩራት ይሰማናል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፡-ደማችንን በመለገስ የወገኖቻችንን ህይወት መታደግ በመቻላችን ኩራት ይሰማናል ሲሉ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች ገለጹ፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች  "ደሜ ለወገኔ" በሚል መሪ ሃሳብ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የደም ልገሳ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡ 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ እንደተናገሩት፤ አገልግሎቱ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በንቃት እየተወጣ ይገኛል፡፡


 

የዛሬው የደም ልገሳ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ለአቅመ ደካሞች ማዕድ ማጋራት፣ ወላጅ ላጡ ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ የማሟላትና መሰል ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት የትምህርትና ቅስቀሳ ባለሙያ ሲሰተር አሰጋሽ ጎሳ፤ ማንኛውም ጤነኛ የሆነና ከ18 እስከ 65 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝና የሰውነት ክብደቱ ከ45 ኪሎ ግራም በላይ የሆነ ሰው ደም መለገስ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡


 

የሚለገሰው ደም በወሊድ፣ በድንገተኛ አደጋ፣ በካንሰር እና በተለያዩ ቀዶ ህክምና ምክንያት ለደም እጦት ለተጋለጡ ወገኖች የሚውል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ደም ከለገሱ የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ሰራተኞች መካከል አቶ ሙሉቀን አየነው በዓመት አንድ ጊዜ ደም ሲለግሱ መቆየታቸውን አውስተው፥ በቀጣይ በዓመት ሶስት ጊዜ ለመለገስ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

አቶ ሚሊዮን ጌታቸው በበኩላቸው ደም መለገስ በደም እጦት ለሚሰቃዩ ወገኖች ህይወት መስጠት መሆኑን ጠቅሰው የምለግሰው ደም ህይወት የሚታደግ በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም