የሻደይ በዓልን ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በአብሮነት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሻደይ በዓልን ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በአብሮነት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

ሰቆጣ ፤ ነሐሴ 1/2017 (ኢዜአ)፡ - በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሻደይ በዓልን ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በአብሮነት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ እዮብ ዘውዱ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፤ የአብሮነት ፣ የአንድነት እና የመተባበር እሴት መገለጫ የሆነውን የሻደይ በዓልን ለማክበር ከወዲሁ ቅድመ መሰናዶ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ በአደባባይ በሰቆጣ ከተማና በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ እንደሚከበር ገልጸዋል።
በዓሉ ጥንታዊነቱንና ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በመንደር፣ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ልጃገረዶች በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ተውበው በዓሉን ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
የዘንድሮው የሻደይ በዓል በባህል ፌስቲቫልና በሌሎች ዝግጅቶች ታጅቦ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል።
ሻደይን ለመታደም ለሚመጡ የሃገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ምቹ የሆቴል እና የመዝናኛ ስፍራዎች መዘጋጀታቸውንም አቶ እዮብ አንስተዋል።
በሰቆጣ ወረዳ የሽመድር ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አለምናት ቢበይን በሰጠችው አስተያየት፤ የሻደይ በዓል በጉጉትና በፍቅር የምንጠብቀው ታላቁ ባህላችን ነው ብላለች።
የዘንድሮውን ሻደይ በዓል እንደወትሮው ሁሉ በደመቀ መልኩ ለማክበር የሻደይ ቀሚስ፣ ድሪ ፣ማርዳ፣ መስቀልና የመሳሰሉ ጌጣጌጦችን ገዝታ ማዘጋጀቷን ተናግራለች።
ሻደይ ከነፃነት ባለፈ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የመተባበርና የመተጋገዝ እሴት ያለው በመሆኑ የምናፍቀው በዓል ነው ያለችው ደግሞ በወረዳው የቲያ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት መቅደስ ሞላ ናት፤።
የዘንድሮውን የሻደይ በዓል በደመቀ መልኩ ለማክበር ከሌሎች የአካባቢው ሴቶች ጋር ቡድን መስርተው ለበዓሉ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁማለች።