በካፋ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ለቱሪስቶች ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነው

ቦንጋ ፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ) ፡-በካፋ ዞን የሚገኙ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ለቱሪስቶች ክፍት ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2017 ዕቅድ አፈጻጻም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ ላይ ያተኮረ መድረክ አካሂዷል።

 

የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ታሪኳ ታከለ፣ በዞኑ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች እንዳሉ ጠቅሰው፣ መዳረሻዎችን የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማልማትም የዞኑ አስተዳደር በመደበው 18 ሚሊዮን ብር በጊምቦ ወረዳ ዳዲበን ፍል ውሃ እና በዴቻ ወረዳ የእግዜር ድልድይን በማልማት ለጎብኚዎች ክፍት መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የባርታ ፏፏቴን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ወይዘሮ ታሪኳ የገለጹት።

ከእነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚገኝ ገቢን ከማሳደግ አንጻር ክፍተት መኖሩን ጠቁመው፣ በቀጣይ መዳረሻዎችን ከማስተዋወቅና ከመጠበቅ ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ሥራ ይጠናከራል ብለዋል። 

በዞኑ 128 የቱሪስት መስህቦችን የመለየት ሥራ መሰራቱን የገለጹት ወይዘሮ ታርኳ፣ ከእነዚህ ውስጥ 28ቱ ባህልና ቅርስን የሚያስተዋውቁ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የተፈጥሮ መስህቦች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዞኑን ህዝብ ባህልና ቋንቋ ለማሳደግና ለማስተዋወቅ በየደረጃው በተሰሩ ሥራዎችም ውጤት እየታየ መሆኑን ሃላፊዋ ተናግረዋል።

በዞኑ የሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን በአግባቡ ለይቶ በማልማት ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እንዲኖረው የተሰጠው ትኩረት እንደሚጠናከር የገለጹት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የካፋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ ወይዘሮ ጽዮን ታዬ ናቸው።


 

ዞኑ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች መገኛ ቢሆንም ለጎብኚዎች ክፍት ሳይሆኑ እና በተገቢው ሳይተዋወቁ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት እየታየ ይገኛል ብለዋል።

የቱሪስት መዳረሻዎችን ለሥራ እድል ፈጠራና ገቢ ማስገኛ ለመጠቀም በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት ወይዘሮ ጽዮን፣ ለዚህም አስጎብኚ ድርጅቶችን ማቋቋምና መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም የማህበረሰቡን ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ በጥናትና ምርምር ታግዞ በማልማት ለህዝቦች ትስስርና ለሰላም እሴት ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመድረኩ ከዕቅድ አፈጻጸምና ትውውቅ በተጨማሪ የካፊቾ ዘመን መለወጫ "መሽቃሬ ባሮ" ላይ ያተኮረ የንቅናቄ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም