በኮምቦልቻ ከተማ ገበያን በማረጋጋት ረገድ የተገኘው ውጤት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ

ደሴ ፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ፡-በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ገበያን በማረጋጋት  ረገድ የተገኘው ውጤት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ  አስታወቁ። 

የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በ2017 በጀት ዓመት ገበያውን በማረጋጋቱ ተግባር ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ነጋዴዎች የእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓትና የምክክር  መድረክ አካሂዷል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይ የንግዱን ማሕበረሰብና ሸማቹን የሕብረተሰብ ክፍል በማስተባበር ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ የተደረገውን ጥረት አድንቀው፤ በአዲሱ የስራ ዘመንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ምርት ካለበት አካባቢ በማምጣት በስፋት እንዲቀርብ የሚደረገውን ጥረት የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮናስ መላኩ በበኩላቸው፤  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ምርት በስፋት በማቅረብ ገበያው እንዲረጋጋ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።


 

የተለያዩ ባዛሮችን በማዘጋጀት፣ የእሁድ ገበያና ጊዜያዊ የገበያ ማዕከላትን በማመቻቸት ከ130 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በወቅቱ እንደቀረቡ አውስተዋል።

ገበያ በማረጋጋት በጎ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ዛሬ የተሰጠው እውቅናም በቀጣይም መልካም ተግባራቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

እውቅና ካገኙ ነጋዴዎች መካከል አቶ አረጋ ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት፤  ጤፍ፣ ዘይትና ስኳር በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።


 

ዛሬ የተሰጠኝ እውቅናም ቀጣይ የበለጠ እንድሰራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ምርት በብዛት በማቅረብ ገበያው እንዲረጋጋ ኃላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁና ቁርጠኛ ነኝ ብለዋል።

አቶ ሰይድ አሊ በበኩላቸው፤ " ቦርከና "  አትክልትና ፍራፍሬ ማህበር አቋቁመው ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ብርቱካንና ሌሎችንም ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ በሚያዘጋጀው ባዛርና ጊዜያዊ ገበያ ምርት በስፋት በማቅረብ ገበያው እንዲረጋጋ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አውስተው፤ ያገኘነው እውቅናም የበለጠ እንድንሰራ የሚያበረታታ  ነው ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶች፣ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም