በአረንጓዴ ዐሻራ የተከልናቸው ችግኞች ለውጤት እንዲበቁ እንንከባከባለን - የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሰራተኞች

ባህርዳር፤ ነሐሴ 1/2017 (ኢዜአ)፡ -በአረንጓዴ ዐሻራ  መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ  የተከሏቸው ችግኞች ፀድቀው  ለውጤት እንዲበቁ ተከታትለው እንደሚንከባከቡ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሰራተኞች  ገለጹ።

የቢሮውና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በአማራ ህዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል ቅጥር ግቢ ዛሬ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ከተሳተፉት መካከል አቶ መልካሙ አዳም በሰጡት አስተያየት፤ በማዕከሉ ግቢ ሀገር በቀል፣ ለምግብነትና ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ችግኞችን መትከላቸውን ተናግረዋል።  


 

የተከሏቸው ችግኞች አካባቢውን ከማስዋብ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም  የሚረዱ፤ ቱሪስቶች የሚያርፉባቸውና ቆይታቸውም ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ችግኞቹ ፀድቀው ለውጤት እንዲበቁም በቀጣይ የአረም፣ ኩትኳቶና ውሃ የማጠጣቱን ተግባር ትኩረት ሰጥተው በማከናወን እንደሚንከባከቡ  አስታውቀዋል።

ወይዘሮ አስካል አምባቸው በበኩላቸው፤ ዛሬ የተከሏቸውን ችግኞች እንደልጆቻቸው ተንከባክበው ለማሳደግ እንደሚጥሩ ገልጸዋል።


 

ችግኝን ተንከባክቦ ማሳደግ አካባቢን  ውብ፣ ሳቢና ማራኪ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ቀደም ሲል የተከሏቸውን ችግኞችም ተከታትለው  በማረምና በመኮትኮት ለውጤት ማብቃታቸውን አውስተዋል።

ለምግብነትና ለባህል መድኃኒትነት የሚውሉ ሀገር በቀል ችግኞችን መትከላቸውን  የተናገሩት ደግሞ ሌላው የተቋሙ ሰራተኛ  አቶ አበበ እምቢያለ ናቸው።


 

የምንተክላቸው ችግኞች የምንተነፍሰው አየር፣ የምንመገበው ምግብና ከህይወታችን ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው መትከል ብቻ ሳይሆን ፀድቀው ለውጤት እንዲበቁ እንንከባከባለን ሲሉ ገልጸዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ፤  ዛሬ በአማራ ህዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል ቅጥር ግቢ የተከሏቸው ችግኞች ዘርፈ ብዙ  ጠቀሜታ ያላቸው  መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሀገር የምታንሰራራው፣ በረሃማነትን መከላከል የምንችለው፣ የአፈር መከላትን የምንከላከለውና የምግብ ዋስትናችንን በዘላቂነት ማረጋገጥ የምንችለው ችግኝን በመትከልና ተንከባክበን ስናሳድግ ነው ብለዋል።

ዛሬ የተከሏቸው ችግኞች ሀገር በቀልና ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነትና ለዕደጥበብ ስራዎች የሚያገለግሉ  እንደሆኑ አስረድተዋል፤


 

ችግኞች የተከሉበት ግቢ አንዱ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆኑ ፀድቀው እንዲያድጉ ተንከባክበው የመጠበቁን ስራ አጠናክረው  እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም