በክልሉ የመጣውን ሰላም የማጽናትና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የመጣውን ሰላም የማጽናትና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ባሕርዳር፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የመጣውን ሰላም የማጽናትና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የክልሉ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አስቻለ አላምሬ፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር ረገድ በጽህፈት ቤቱ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ መሆኑን አንስተው የህዝቡ ትብብር እንዲሁም የጸጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት የተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት የሚሊሻ አባላት ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተሳካና ውጤታማ የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ ማከናወናቸውን አስታውሰዋል።
በመሆኑም በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የህግ ማስከበር ስራው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የህግ ማስከበር ስራው እንዳለ ሆኖ የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በርካታ የፅንፈኛው ቡድን አባላት ትጥቃቸውን በመፍታት ህዝቡን እየተቀላቀሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመጣው ውጤት በመንግስት ያላሰለሰ የሰላም ጥረት፣ በኃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም አጠቃላይ የህብረተሰቡ እገዛ መሆኑን አስታውሰው የጽንፈኛውን የጥፋት ዓላማ በቅጡ እየተረዱ በርካቶች ወደ ሰላም የተመለሱ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ የመጣውን ሰላም አፅንቶ ልማትን ለማስቀጠል የሕዝቡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አሁንም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው የሰላም ማፅናትና የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።