የኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በዓለም አቀፍ መድረክ ትብብራቸውም የበለጠ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል - ፕሬዝደንት ታዬ አፅቀስላሴ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በንግድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክም ትብብራቸው የበለጠ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

የ2025 የቻይና የህክምና በጎ ፈቃደኞች የአፍሪካ በጎ አድራጎት ተልዕኮ እና አለም አቀፍ የህክምና በጎ ፈቃደኞች ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሲልክ ሮድ ጠቅላላ ሆስፒታል ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ ተገኝተዋል።


 

በመርሃ ግብሩ የተለያዩ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች፣ የልጆች የልብ ቀዶ ሕክምና፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ የዐይን ህክምና እና የማህፀን ቀዶ ሕክምና እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

በተጨማሪም በአንድ የመንግስት እና በአንድ የግል ትምህርት ቤት የዓይን እና የልብ ምርመራ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

እንዲሁም ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ እንደሚደረግም ተጠቁሟል።


 

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ወቅት የቻይና በጎ ፈቃደኞች ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ በርካታ ልጆችና ተጨማሪ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው

አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ በቆይታቸው ለእውቀት እና ክህሎት ሽግግር ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ እና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በንግድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክም የበለጠ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በቻይና በጎ ፈቃደኛ ሀኪሞች የሚካሄደው መርሃ ግብር ከቻይና ህዝቦች ጋር ለዘመናት የቆየ አጋርነት አብሮነት እና የዕድገት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና አገልግሎት ድንበር እንደሌለው ገልጸው፤ የዛሬው መርሃ ግብር ለሁሉም ሰው ጠንካራ መልዕክት እንዳለው ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሁሉም በላይ ርህራሄ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት በክረምት የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

በዘንድሮው ክረምትም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ችግረኛ የሆኑ አምስት ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረስ መታቀዱን ጠቁመዋል።

የቻይና በጎ ፈቃደኛ ሀኪሞችም በዚህ የበጎነት ተግባር በመሳተፋቸው ምስጋና አቅርበዋል።


 

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ቻይና እና አፍሪካ በቅርብ ጥሩ ወዳጆች፣ አጋሮች እና ወንድማማቾች ናቸው ብለዋል።

የቻይና እና የአፍሪካ የጤና ትብብር ይበልጥ እየጠነከረ መምጣቱን ገልጸው፤ አጋርነታቸውም ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ተናግረዋል።

የጤና ትብብራቸውም እየሰፋ እና ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም