በክልሉ በኢንዱስትሪ እና በግብርና ልማት ዘርፎች የታየው ማንሰራራት በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ማስካት የሚያስችል ነው

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በኢንዱስትሪ እና በግብርና ልማት ዘርፎች የታየው ማንሰራራት በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማሳካት የሚያስችል መልካም ጅማሮ መሆኑን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትንና እየተመዘገበ ያለውን ውጤት በተመለከተ የቢሮው ኃላፊ አራርሶ ገረመው (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ዶክተር አራርሶ በማብራሪያቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በብዙ ማሳያዎች እመርታ እና ጥሩ ተስፋ የተሰነቀባቸው የተለያዩ ዘርፎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።


 

በተለይ በኢንዱስትሪ እና በግብርና ልማት ዘርፎች የታየው ማንሰራራት በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ማስካት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፣ የ2018 በጀት ዓመት ደግሞ ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን የምንሻገርበት ይሆናል ብለዋል።

በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የሚመረቱ የአቮካዶ ዘይትና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶች የለውጥና የሽግግር ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የአቮካዶ ምርፍት ከቡና ቀጥሎ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ከ146ሺህ 400 ለሚልቁ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጨባጭ ለውጥና ውጤት የመጣበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በጤናና በትምህርት፣ በገጠር መሰረተ ልማትና የመንገድ ተደራሽነትን በማስፋት እንዲሁም የውሃና የኤሌክትሪክ አገልገሎትን በማሳለጥ በኩል ጥሩ ጅምሮች እንዳሉም ዶክተር አራርሶ ገልጸዋል።


 

በቀጣይም በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ልማትና ከቤተሰብ ጀምሮ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

በክልሉ ምክር ቤት ዘንድሮ ከጸደቀው 32 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በጀት ውሰጥ 63 በመቶ የሚሆነው ለድህነት ቅነሳ የሚውል መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም