ኢትዮጵያ የስታትስቲክስ ስርዓትን ለማጠናከር እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው - የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የስታትስቲክስ ስርዓትን በማጠናከር በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔ ለመስጠት እያከናወነችው ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታወቀ።

አፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የስታትስቲካል ስርዓትን ማጠናከር ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባትም ተጠቁሟል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ ስታትስቲክስ ማዕከል ተጠሪ ቲንፊሲ ጆሴፍ ኢልቦውዶ ለኢዜአ እንዳሉት የግብርና መረጃዎች ቀጣይነት ላለው የግብርና ስርዓት መሰረት ናቸው።

በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በስነ-ህዝብና በሌሎች ዘርፎች የተደራጀ የስታትስቲክስ መረጃ መኖር በጥናት ላይ የተመሰረተ የልማት እቅድና የፖሊሲ ውሳኔ ለመስጠት መሰረት መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በስታትስቲክስ መረጃ አስተዳደር አበረታች ስራዎችን እያከናወነች እንደሆነም ተናግረዋል።

አንድነቷ የተጠናከረ፣ የበለጸገችና ዘላቂ ሰላም የተረጋገጠባት አፍሪካን እውን ለማድረግ የአጀንዳ 2063ን ጨምሮ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙም አንስተዋል።

በተለይም በአህጉሪቱ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለምጣኔ ሃብት መሰረት በሆነው ግብርና የተደራጀና ጠንካራ የመረጃና ስታትስቲክስ አቅርቦት ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።

የምግብ ፍጆታ የሚያስፈልገው ህዝብ ብዛት፣ የማምረት አቅም፣ በምርትና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ የተጠናቀረ መረጃ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

አፍሪካ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔ በመስጠት የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ መረጃን በመሰብሰብ፣ በመተንተንና በጥናት በማረጋገጥ የስታትስቲክስና መረጃ ስርዓቷን ለማጠናከር ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም በአህጉሪቱ ያለውን ወጣት የሰው ሃይል አቅም በማጎልበትና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በአፍሪካ ጠንካራ የመረጃና ስታትስቲክስ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት በሀገራት መካከል ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነም ጨምረው አንስተዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ ስታትስቲክስ ማዕከል የግብርና ስታትስቲክስ መረጃዎችን ጨምሮ ጠንካራ የመረጃ ማዕከልን ለመገንባት አቅም ማጎልበት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም