የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፦ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ፈጣንና ውጤታማ ለማድረግ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ዝግጅት ማጠናቀቁን የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ 1ሺህ 122 የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ቀርበው መርምሮ ውሳኔ መስጠቱንም አስታውቋል።

የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ወይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሕገ መንግስት ጥሰት ተፈጥሮብኛል በሚል ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ምርመራ እና ጥናት በማድረግ ፈጣን ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከቀረቡለት 1ሺህ 122 መዝገቦች የተለያዩ ውሳኔዎችን መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም 32 መዝገቦች የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ጉባኤው ውሳኔ በመስጠት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስተላለፉን አስታውቀዋል፡፡

ውዝፍ ፋይሎችን ጨምሮ የተቀሩትን መዝገቦች መርምሮ የህገ መንግስት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ሲል ውሳኔ ማሳለፉንም ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት አመት ፋይሎችን በመመርመር በፍጥነት ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ በጀት ዓመት የበለጠ ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ለዚህም ተቋሙ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አንስተው፤ በተያዘው ነሐሴ ወር ወደ ስራ ይገባል ብለዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ አቅሙን ለማሳደግ እና ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የአህጉር እና የዓለም አቀፍ የህገ መንግስት ፍርድ ቤቶች አባል በመሆን በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም