የሁለት ጊዜ የቻን አሸናፊዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከዛምቢያ ጋር ትጫወታለች 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1 /2017(ኢዜአ)፦ በስምንተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) የምድብ አንድ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

ከጨዋታዎቹ መካከል በኬንያ ንያዮ ስታዲየም ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከዛምቢያ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ይገኝበታል።

የቻን ውድድርን ሁለት ጊዜ ያሸነፈችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ በኬንያ 1 ለ 0 ያስተናገደችው ሽንፈት ያልተጠበቀ ነበር። 

በአንጻሩ ተጋጣሚዋ ዛምቢያ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

ሁለቱ ቡድኖች በቻን ውድድር ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። 

ኮትዲቭዋር እ.አ.አ በ2009 ባዘጋጀችው የመጀመሪያ የቻን ውድድር በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 2 ለ 1 አሸንፋ ለፍጻሜ ያለፈች ሲሆን በፍጻሜውም ጋናን በመርታት ታሪካዊውን ዋንጫ አንስታለች።

ከቻን ውጪ ባደረጓቸው ሁለት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።  

ሁለቱ ሀገራት በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ለማሸነፍ የሚያደርጉት ፍልሚያ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይበቃል። 

በዚሁ ምድብ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ኬንያ ከአንጎላ በካሳራኒ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በውድድሩ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ያደረገችው ኬንያ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 1 ለ 0 ረታለች። አንጎላ በሞሮኮ 2 ለ  0 ተሸንፋለች። 

ሁለት ሀገራት በቻን ውድድር ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አራት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል።

ጨዋታው ኬንያ በድሏ ለመቀጠል በአንጻሩ አንጎላ ከሽንፈቷ በኋላ ምላሽ ለመስጠት የሚያደርጉት መሆኑ ተጠባቂ ያደርገዋል።

ቻን ኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ያዘጋጁት አህጉራዊ የእግር ኳስ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም