ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን
መቱ፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፦ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን የቦንድ ግዥና የገንዘብ ልገሳ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኦሮሚያ ክልል የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታረቀኝ ዓለማየሁ የግድቡ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን በየዓመቱ ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አሁንም የግድቡን ምርቃት ዜና በጉጉት እየጠበቁ ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሶፊያ ጀማል ከአካባቢያቸው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ለግድቡ ግንባታ በተከታታይ ቦንድ በመግዛት ሲሳተፉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ዘንድሮም ቦንድ መግዛታቸውን ጠቅሰው ሌሎችም በግድቡ ግንባታ ሂደት አሻራቸውን እንዲያኖሩ እያስተባበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለሕዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እና ድጋፍ መቀጠላቸውን የሚገልጹት ደግሞ አቶ ጥላሁን ተካ ሲሆኑ አሁንም ግድቡ እስኪመረቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በዞኑ ለሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በሕብረተሰብ ተሳትፎ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቶለሳ አሰፋ ናቸው።
በተያዘው ክረምትም 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው እስካሁን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡንም አብራርተዋል።
በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ለግድቡ ግንባታ በሕብረተሰቡ የሚደረገው ድጋፍ እስከፍጻሜው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።