ኢንስቲትዩቱ ለሀገራዊ እድገት ግቦችን መሰረት ያደረጉ የምርምርና ስልጠና ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ ለሀገራዊ እድገት ግቦችን መሰረት ያደረጉ የምርምርና ስልጠና ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ሀገራዊ የእድገት ግቦችን መሰረት ያደረጉ የምርምርና ስልጠና ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በድሬዳዋ በ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃጸም ግምገማና በተያዘው በጀት አመት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አመራሮች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በተያዘው በጀት አመት ጥራትን ማዕከል በማድረግ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ብለዋል።
የኢንስቲትዩቱ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ጌትነት ተሾመ እንዳሉት፤ ተቋሙ ሀገራዊ ተልዕኮውን በስኬት ለመወጣት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በተለይም ሀገራዊ የኢኮኖሚ ምሰሶዎችን መሰረት ያደረጉ የምርምርና ስልጠና እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ውጤታማ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው በጀት አመትም ጥራትን ማዕከል በማድረግ ሀገራዊ ተልዕኮ በማንገብ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በድሬዳዋ የተካሄደው ግምገማ በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ የምርመርና ስልጠና ስራዎችን ለማከናወን ጥሩ መደላድል የተፈጠረበት መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ የጥራት ማረጋገጥ(ኳሊቲ አሹራንስ) ዳይሬክተር ኃይለማርያም ምትኩ(ዶ/ር) ናቸው።
በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር፣ በቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዞች ልማት እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል በመሆን ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት ጥቅሞች በላቀ ደረጃ የማሳደግ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።