ቀጥታ፡

ታታሪውን የካሜራ ባለሙያ የዘከረው የስነ-ጽሁፍ ምሽት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየወሩ በቋሚነት የሚከናወን ተቋማዊ የስነ ጽሁፍ ምሽት አስጀምሯል።

መድረኩ በዛሬው መርሃ ግብሩም ‘’ታታሪነትን ማወደስ” በሚል መሪ ሃሳብ በቅርቡ በድንገተኛ አደጋ ሕይወቱ ያለፈውን የካሜራ ባለሙያ ብዙዓየሁ ብርሃኑን ዘክሯል።

በዛሬው የስነ-ጽሁፍ መድረክ የተቋሙ ሰራተኞች በግጥም፣ በወግ እንዲሁም አጫጭር ልብ ወለዶች ታታሪውን የካሜራ ባለሙያ ብዙዓየሁ ብርሃኑን ዘክረዋል።


 

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ወርሃዊ የስነ-ጽሁፍ ምሽቱ ተቋማዊ የእርስ በርስ መቀራረብን በማጠናከር ጠንካራ የስራ ባህል ለማጎልበት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የስነ ጽሁፍ አቅም እያላቸው ዕድሉን ያላገኙ ሰራተኞች ያላቸውን ተሰጥኦ የሚገልጡበት መድረክ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የመጀመሪያው መድረክ በሙያውም ሆነ በባህሪው ምስጉንና ታታሪ የነበረውን ብዙዓሁ ብርሃኑን በመዘከር መካሄዱንም አድንቀዋል።


 

ብዙዓየሁ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በነበረው የስራ ስምሪት በሙያው የተመሰከረለትና ለሀገር ታላላቅ ስራዎችን ያበረከተ ባለሙያ እንደነበርም አንስተዋል።

ታታሪነትን ማወደስ በስራቸው ምስጉን ሰራተኞችን ለመፍጠር ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህ አኳያ መድረኩ የብዙአየሁ ጠንካራ የስራ ክህሎት በሌሎች ሰራተኞች መነሳሳትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።


 

በመድረኩ የሚቀርቡ የስነ ጽሁፍ ስራዎችም ተመርጠው በአንድ መድብል እንዲታተሙ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ቀጣዩ የስነ-ጽሁፍ መድረክም በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ የሚከናወን ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም