የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትና የፈጠራ አቅማችንን ለማዳበር እያገዘን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትና የፈጠራ አቅማችንን ለማዳበር እያገዘን ነው

ዲላ፤ ሐምሌ 30/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትና የፈጠራ አቅማቸውን ለማዳበር እያገዛቸው መሆኑን በዲላ ከተማ የኢትዮ ኮደርስ ሰልጣኞች ገለጹ።
በከተማ አስተዳደሩ ከ3ሺህ 500 በላይ ዜጎች የሚሳተፉበት የክረምት ወራት የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ማስጀመሪያ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
ከከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ሠራተኞች መካከል አቶ ሚካኤል ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ሲል በወሰዱት የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ እውቀት መጨበጣቸውን ገልጸዋል።
ይህም የመንግስት ሥራቸውን በቴክኖሎጂ ታግዘው ለማከናወን ዕድል ከመፍጠሩና የዲጂታል ክህሎታቸውን ከማዳበር በሻገር ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በፋንዳሜንታል ፕሮግራምና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስዳ ማጠናቀቋንና በዚህም የፈጠራ አቅሟን ማሳደጓን የተናገረችው ደግሞ ተማሪ መልካም አስራት ናት።
ለዚህም ቃላትን፣ ተንቀሳቃሽ ምስልና ፎቶዎችን ያካተተ የቋንቋ መማሪያ ሶፍት ዌር ማበልጸጓን ጠቅሳለች።
ሶፍት ዌሩ ጀማሪ ሕጻናትን ሳቢ በሆነ መንገድ የአካባቢና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን በቀላሉ እንዲማሩ የሚረዳ መተግበሪያ መሆኑንም ገልጻለች።
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የፈጠራ አቅሟን ከማጎልበት በተጨማሪ ለቀለም ትምህርቷ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዓለምን ለመረዳት እያገዛት መሆኑን ተናግራለች።
የዲላ ከተማ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ኢሣያስ ተፈራ በበኩላቸው በከተማው ባለፈው ዓመት 1ሺህ 951 ሰዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደዋል ብለዋል።
በተያዘው የክረምት ወራትም 3ሺህ 502 ዜጎችን ለማሰልጠን ዝግጅት መደረጉን አንስተው፣ በስልጠናው የኔትወርክ መሰረተ ልማት ውስንነት እንደይገጥም ስድስት ማዕከላት መደራጀታቸውን ገልጸዋል።
በስልጠናው ወጣቶች፣ የመንግስት ሠራተኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጎን ለጎን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በመውሰድ ራሳቸውን እንዲያበቁ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የከተማው ነዋሪዎች በስልጠናው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መፋጠን የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ያነሱት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ(ዶ/ር) ናቸው።
በተለይ የኮደረስ ስልጠና ዲጂታል እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በማሳደግ የሀገር ውስጥና የውጪ ሥራ እድል ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሰፋ ገልጸዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ በኮዲንግ ስልጠና አቅሙንና ክህሎቱን በመሳዳግ ለዲጂታል ዓለም ብቁ ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የክረምት ወራት የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ከማስጀመር በተጨማሪ ቀደም ሲል ስልጠናቸውን ወስደው ላጠናቀቁ ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።